በአዲስ አበባ ከተማ በተሽከርካሪዎች ግጭት ምክንያት ከ 9.1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመንገድ ሀብት ላይ ጉዳት ደርሷል

በተጠናቀቀው 2013 በጀት ዓመት ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በቀለበት መንገድ እና ከቀለበት መንገድ ውጭ ባሉት መንገዶች ላይ በተሽከርካሪዎች ግጭት ምክንያት ብቻ ከ 9.1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመንገድ ሀብት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

በበጀት ዓመቱ 12 ወራት ውስጥ 62 ግጭቶች በቀለበት መንገድ በሚገኙ ሀብቶች ላይ ሲደርስ 310 ግጭቶች ደግሞ ከቀለበት መንገድ ውጪ በድምሩ 372 የሚሆኑ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

ከፍተኛ የሀገር ሀብት ፈሶባቸው በተገነቡ የመንገድ አውታሮች ላይ በየጊዜው በተሽከርካሪዎች ግጭት እየደረሰ ያለው ጉዳት በአጠቃላይ የትራፊክ እንቅስቃሴው ላይ ከሚያሳድረው ተፅዕኖ በተጨማሪ የሀገርን ኢኮኖሚ ለኪሳራ መዳረግ ነው፡፡

አብዛኛውን ጊዜ በግጭት ጉዳት እየደረሰባቸው የሚገኙት የመንገድ ሀብቶች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተገዝተው በምሽት አገልግሎት እንዲሰጡ በተተከሉት የመንገድ ዳር መብራት ምሰሶዎች፣ የትራፊክ ምልክቶች፣ የአቅጣጫና ርቀት አመላካች ሰሌዳዎች፣ የእግረኛ መከላከያ አጥሮች፣ የመንገድ ማካፈያ ግንቦችና የውሃ መውረጃ ቱቦዎችና ክዳኖች ላይ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን መንገዶቹ ላይ የደረሰውን ጉዳት መልሶ በመጠገን ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረግ ስለሚኖርበት ተመጣጣኝ የሆነ የካሳ ክፍያ ጉዳት አድራሾቹ ሙሉ በሙሉ እንዲከፍሉ አድርጓል፡፡

በከተማዋ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ በአግባቡ ለማሳለጥ እና የከተማዋን ገፅታ ለማሻሻል መንገዶች ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ የመንገድ ሀብቶችን ከጉዳት በመጠበቅና በመንከባከብ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንዳለበት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጰያውያን
ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.