ከተከራየበት ቦታ ሰኔ 30 2013 ዓ.ም ሊፈናቀል የነበረው የሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር፤ እስከ የካቲት 30 2014 መቆየት የሚችልበትን ፈቃድ ማግኘቱን ገለፀ

ከሁለት አስርት አመታት በላይ ተከራይቶ ችግረኞችን ሲረዳ ከነበረበት ቦታ ሰኔ 30 2013 እንዲለቅ በመገደዱ ተረጂዎችን የመበተን አደጋ ተጋርጦበት የነበረው ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር ፤ እስከ የካቲት 30 2014 መቆየት የሚያስችለውን ፈቃድ ከባለቤቱ ማግኘቱን ገልጧል፡፡

የሙዳይ ቦጎ አድራጎት ማህበር መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ሙዳይ ምትኩ ለጣቢያችን እንደተናገሩት አከራያችን አቶ አህመድ መሐመድ ቦታውን ሊሰራበት ስለፈለገ እንድንለቅ ሲነግረን የነበረው ከ 2 አመት ወዲህ ነው፡፡

ሆኖም ግን ዘንድሮ ከ ሰኔ 30 2013 እንደማናልፍ ነግሮን የነበረ ቢሆንም፤ አብሮ አደጉን ኡስታዝ አቡበከርን ጨምሮ 10 ሽማግሌዎች ልከንበት፣ ሽማግሌዎቹን ሰምቶ እስከ የካቲት 30 2014 ሊያራዝምልን ቃል ስለገባ ልናመሰግነው እንወዳለን ብለዋል፡፡

ሙዳይ ለከተማ አስተዳደሩ የቦታ ጥያቄ አቅርቦ ፤የይገባኛል ጥያቄ የሌለበት የፀዳ 2 ሺህ ካ.ሜ ቦታ ተብሎ በቀድሞ የካ ክ/ከተማ፣ በአሁን ለሚ ኩራ ክ/ከተማ ውስጥ የተካለለ ቦታ ቢሰጠውም፤ ቦታው ግን አርሶ አደሮች የሚጠቀሙበት፣ ይገባኛል ያለበት ቦታ ሆኖ መገኘቱ ሙዳይ ተከራይቶ የኖረውን ቤት በፍጥነት እንዳይለቅ ከባድ አድርጎበታል፡፡

አርሶ አደሮቹ በቦታው ላይ ለማልማት ጥያቄ ያቀረቡ፣ መነሳት የማይፈልጉ በመሆናቸው፤ ሙዳይ ሌላ ምትክ ቦታ ጠይቋል፡፡

የካቲት 30 2014 ነገ ትደርሳለች የሚሉት ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ ቦታውን በፍጥነት አግኝተን ፣ የስራና የማደሪያ ቦታዎችን ከህዝቡ ጋር በጋራ ሰርተን ፤ከበቂ በላይ ጊዜ በትዕግስት ሰጥቶ የጠበቀንን አከራያችንን አመስግነን ቤቱን መልቀቅ አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ለማ ፤ለጣቢያችን የሙዳይን ሁኔታ እንረዳለን፣ አርሶ አደሮቹ ለቦታው ከዚህ ቀደም ካሳ መውሰድ አለመውሰዳቸውን አጣርተን፤ ወይ ለነሱ ካሳ ሰጥተን ቦታውን ለሙዳይ እናስረክባለን ወይ ለሙዳይ ምትክ ቦታ እንፈልጋለን ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡

የሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር በአሁኑ ሰዓት በቀጥታ በማዕከሉ የሚኖሩ 450 ሴቶችንና 650 ሕጻናትን የሚንከባከብና የሚያስተምር ማኅበር ነው።

እስካሁን በቀጥታ ከ 3 ሺህ በላይ፣ በተዘዋዋሪ ከ7 ሺህ በላይ ልጆችን የረዳ ሲሆን 1300 ሴቶች ድነውና ራሳቸውን ችለው ከማዕከሉ ወጥተዋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።

ሔኖክ አሥራት
ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *