የሕዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የኢትዮጵያዊያን ልዩ የድል ብስራት ቀን ነው ሲሉ ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡

“የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የኢትዮጵያዊያን ልዩ የድል ብስራት ቀን ነው” ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ የግድቡ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

“የግድቡ ውሃ ሙሌት አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ ኢትዮጵያዊያን በከፍተኛ ቁርጠኝነትና ትብብር ሰርተዋል”ያሉት ጀነራል ብርሃኑ፤ ግድቡ የሞላበት የዛሬው እለት “የኢትዮጵያዊያን ልዩ የድል ብስራት ቀን ነው” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ማንንም አገር የመጉዳት ፍላጎትና ዓላማ እንደሌላት ገልጸው፤ የግድቡ የውሃ ሙሌትም ይህንን በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ አክለውም የሕወሃት አሸባሪ ቡድን መንግስት ለትግራይ ሕዝብ የሰጠውን የጥሞና ጊዜ በመጠቀም ትንኮሳዎችን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ለትግራይ ህዝብ ደንታ ቢስ መሆኑና ህዝቡን ለከፋ ችግር ለመዳረግ ቆርጦ መነሳቱን አመላካች ስለመሆኑም ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።

“የአገር መከላከያ ሰራዊት ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ በጠንካራ ቁመና ላይ ይገኛል” ብለዋል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ።

በመሆኑም “አሸባሪ ቡድኑ ትንኮሳዎችን የሚቀጥል ከሆነ ሰራዊቱ በሚሰጠው ትዕዛዝ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነው” ሲሉ አረጋግጠዋል።

የትግራይ ህዝብም በተሰጠው የጥሞና ጊዜ በመጠቀም አሸባሪውን የህወሃት ቡድን “ሊዋጋውና በቃህ ሊለው ይገባል” ብለዋል።

ምንጭ፡-ኢዜአ

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.