የንግድ ቤቶቹ መታሸግ ከማንነት ጋር የተያያዘ አንድምታ እየፈጠረባቸው እንደሆነ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ለኢትዮ ኤፍ ኤም ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተፈጠረው ክስተት ጋር በተያያዘም ኑሮአቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የትግራይ ተወላጅ የንግድ ማህበረሰብ አባላት ይህን ያሉት ከጸጥታ አካላት እና ከአዲስ አበባ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡
መከላከያ ሰራዊቱ መቀሌ ከተማን ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ፣በሆቴሎች ፣በመጠጥ ቤቶች ና በምሽት ቤቶች ብጥብጥ ለማስነሳት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦችን በመደገፍ የተጠረጠሩ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱ ይታወሳል፡፡
እርምጃ የተወሰደባቸው እነዚህ ቤቶች በከተማዋ የዘር ፍጅት እንዲከሰት ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች በሆቴል ቤታቸው በማስቀመጥ ድጋፍ አድርገዋል በሚል ነው፡፡
በእለቱ ከነበረው ክስተት ጋር በተያያዘም መንግስት ከስምንት በላይ ባለ ኮከብ ሆቴሎች እና በርካታ ቁጥር ያላቸው ክለቦች እንደዚሁም ምግብ ቤቶችን ጨምሮ በድርጊቱ ተሳትፎ የነበራቸው ከረንቦላ ቤቶች ሳይቀሩ ታሽገዋል፡፡
የንግድ ቤቴ ተዘጋ ተብሎ ቅሬታ ማቅርብ እንዳለ ሁሉ ሀገርም ትፈርሳለች ብሎ መጨነቅ ያስፈልጋል፣ከሁሉ በላይ ግን ሀገር ማስቀደም ከንግዱ ማህበረሰብ ይጠበቃል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ የሴክተር ተቋማት ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት አቶ ሰለሞን ሀይሌ እንዳሉት፣ ሰላማዊ የሆነው የንግዱ ማህበረሰብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ መብቱ ይጠበቃል፤ከንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቀው እራሱን ከጁንታው ቡድን ማራቅ ብቻ ነው ብለዋል፡፡
የትግራይ ተወላጅ የሆነ በሙሉ በሀገር የተከሰተውን ህመም ሊጋራ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ዛሬም ሆነ ነገ የንግዱ ማህበረሰብ ለጥርጣሬ በማይጋብዝ መልኩ የንግድ ስራውን ማከናወን እንዳለበት ነው ሀላፊው የተናገሩት፡፡
መንግስት ከሽብርተኛው ቡድን ጋር ግኑኝነት ያላቸውን ባለሀብቶች እና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት አጣርቶ በቅርቡ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግም አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
በሔኖክ ወ/ገብርኤል
ሐምሌ 21 ቀን 2013 ዓ.ም











