ምርጫው ስለተዘረፈ ፤ የምርጫውን ውጤት በፍፁም እንደማይቀበለው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ገለፀ

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፤ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫን ገምግሞ ውጤቱን ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡
ግምገማው የአዲስ አበባ ምርጫ እና ድህረ ምርጫ ሂደትን የተመለከተ ነው፡፡

በውጤቱም ባልደራስ ፤ገዢው ፓርቲና ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ስለዘረፉት የዚህን ምርጫ ውጤት በፍፁም አልቀበልም ብሏል፡፡

ገዥው ፓርቲ በዋና ፈፃሚነት፤ ምርጫ ቦርድ በተባባሪነት ምርጫውን ስለዘረፉት በፍርድ ቤት ከስሻለሁ ሲል የግምገማ ውጤቱን ይፋ ባደረገበት መግለጫ አሳውቋል፡፡

ይህ ጥናት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ በምርጫ ቀን እና በድህረ ምርጫ ባሉት ቀናት የታዩ ተግዳሮቶችን የሚዳስስ ነው፡፡

እንደ ቅድመ ምርጫ ሂደቱ ጥናት ሪፖርት ውጤት 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ በዕጩዎች፣ በፓርቲው በአባላትና በመራጮች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች (ስድብ፣ ዛቻ እና እስር) እንደተከናወኑበት ከጥናቱ መረጃ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በአንድ የምርጫ ጣቢያ ክልል ከአንድ በላይ ምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው እንደነበር የጥናት ቡድኑ በምርመራ ግኝቱ አመልክቷል፡፡

ይህ ደግሞ ምርጫ ቦርድ ካወጣው ህግ ጋር የሚፃረር ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ከነዋሪው ህዝብ ብዛት ጋር የማይመጣጠኑ እና ቁጥራቸው አነስተኛ እንደነበር ጥናቱ አስገንዝቧል፡፡

የጥናቱ ግኝት እንደሚያሳየው ብዙዎቹ የምርጫ አስፈፃሚዎች የምርጫ እና የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን እንደማያውቁ በጥናቱ አማካኝነት ለመረዳት ተችሏል፡፡

የምርጫ አስፈፃሚዎች የምርጫ እና የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን ጠንቅቀው ላለማወቃቸው ዋናው ምክንያት የምርጫ ቦርድ የምርጫ አስፈፃሚዎች አመላመል ብቃትን ሳይሆን ማንነት መሰረት ባደረገ መልኩ ስለሆነ እንደሆነ የጥናቱ ግኝት ያሳያል፡፡

ስለሆነም የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፤ምርጫው ስለተዘረፈ ፤ የምርጫውን ውጤት በፍፁም አልቀበለውም ብሏል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።

በሔኖክ አስራት
ሐምሌ 23 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *