ከኤሌክትሪክ ኤክስፖርት ከ90 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተጠናቀቀው 2013 በጀት አመት ወደ ወጪ ኤክስፖርት ካደረገው የኤሌክትሪክ ኃይል ከ90 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።

ተቋሙ በአገር ውስጥ ባቀረበው ጅምላ ሽያጭ ከ13 ቢሊዮን 267 ሚሊዮን 104 ሺህ ብር በላይ መሰብሰቡንም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደገለጹት፣ ባለፈው በጀት ዓመት ተቋሙ ከተለያዩ ማመንጫዎች ያመረተውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለውጭና ለአገር ውስጥ ገበያ በጅምላ በማቅረብ ረገድ ከዕቅዱ በላይ አከናውኗል።

በዚህም ለጎረቤት አገራት በበጀት ዓመቱ ካቀረበው የኤሌክትሪክ ኃይል 80 ሚሊዮን 787 ሺህ 600 ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 90 ሚሊዮን 532 ሺህ 669 ዶላር ተገኝቷል።

ይህ ገቢ የተገኘው ለሱዳንና ለጅቡቲ ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሞገስ ከአሁን በፊት በነበሩ የውጭ ገበያ ሽያጮች ከ70 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተሸጠበት ጊዜ አለመኖሩን አስታውሰዋል።

ተቋሙ ለውጭ ከሚያቀርበው ኃይል በተጨማሪ በአገር ውስጥ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ለከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ፋብሪካዎች፣ ለባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት፣ ለኢትዮ-ቴሌኮምና መሰል ተቋማት ኃይል በጅምላ ይሸጣል።

እንደ አቶ ሞገስ ገለጻ፣ በጅምላ ከሚቀርበው የአገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት 13 ቢሊዮን 200 ሚሊዮን 774 ሺህ 591 ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 13 ቢሊዮን 267 ሚሊዮን 104 ሺህ 524 ብር መገኘቱን ኢዜአ ዘግቧል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ሐምሌ 30 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *