የአዲስ አበባ ከተማን የትራንስፖርት ማስተር ፕላን የማሻሻያ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ቢሮ የህዝብ ግኑኙነት ሀላፊ አቶ አረጋዊ ማሩ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት በ3.7 ሚሊዮን ዩሮ ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ የተዘጋጀው ሰነድ ከ2014 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል ብለዋል፡፡

በመዲናዋ እ.ኤ.አ. እስከ 2030 የሚተገበር ሲሆን በከተማዋ ምቹ፣ አስተማማኝና ውጤታማ የተቀናጀ የትራንስፖርት ስርዓት የመዘርጋት ግብ አንግቧል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በበቂ ጥናት ላይ ያልተመሰረተ መሪ አልባ የነበረውን የከተማዋን ትራንስፖርት በማስተር ፕላን የሚመራ የትራንስፖርት ስርዓት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል፡፡

በዚህም መሰረት በመዲናዋ ቀላል ባቡር፣ ሞተርና ፈጣን የከተማ አውቶቡስ ተመጋጋቢ እንዲሆኑ በማድረግ የብዙሃን ትራንስፖርትን ማሳለጥ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

እንዲሁም በትራንስፖርት ዘርፍ የወጡ ሰነዶችንና መሰረተ ልማቶችን የማሻሻል ስራ የሚሰራ ሲሆን በተበጣጠሰ መንገድ የተዘጋጁ ስትራቴጂዎችንም ወደ አንድ ሰነድ ማስተሳሰር ያስችላል፡፡

ሰነዱ በከተማዋ የሚገኙ መንገዶች ለእግረኞች፣ ለብዙሃንና ሞተር አልባ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲውሉ ደረጃቸው እንዲሻሻል ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ ነው ቢሮው ያስታወቀው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የትራፊክ ፍሰትና የመንገድ ደህንነት ማሻሻል የሚያስችሉ ስራዎችም እንደሚሰሩ በሰነዱ ተመላክቷል፡፡

ለጭነት ተሽከርካሪዎች የሚውሉ በከተማዋ አምስቱም መግቢያና መውጫ አካባቢዎች በወለቴ ሱቅ፣ በጎሮ፣ በአቃቂ በሰቃ፣ በቱሉ ዲምቱና በአንፎ ሜዳ ተርሚናሎች ይገነባሉ ተብሏል፡፡

ይህንን ሰነድ ሮምቦል የተባለ የዴንማርክ ኩባንያ የማማከር ስራውን እያከናወነ እንደሚገኝ ነው አቶ አረጋዊ ተናግረዋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።


ሔኖከ ወ/ገብርኤል
ነሐሴ 07 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *