የተፈጠረው የጨው ዋጋ ጭማሪ አፍዴራ ለአንድ ወር ያህል የተመረተው ጨው ባለመነሳቱ ምክንያት የተከሰተ ነው፡፡

በአፋር ክልል አፍዴራ ጥሬ ጨው ለአንድ ወር ያህል አለመነሳቱ የአንድ ኪሎ ጨው ዋጋ ከነበረበት 9 ብር ከ50 በመቶ በላይ ጭማሪ በማሳየት እስከ 20 ብር ለመሸጡ ምክንያት እንደሆነ የተስፋ ለኢትዮጵያ የሸማቾች ማህበር ፕሬዝደንት አስታውቀዋል፡፡

የተስፋ ለኢትዮጲያ የሸማቾች ማህበር ፕሬዝደንት አቶ አስራት በጋሻው ለኢትዮ የንግድ እና ኢንቨስትመንት መድረክ እንደተናገሩት በስፍራው የሚገኙ በጫኝ እና አውራጅነት ላይ የተሰማሩ ሰዎች ቀድሞ በኩንታል ሲከፈላቸው የነበረው 10 ብር ወደ 20 ብር ከፍ እንዲል በመጠየቃቸውና ተረካቢ ፋብሪካዎች በዚህ ባለመስማማታቸው ምክንያት ጨው ለአንድ ወር ያህል ለፋብሪካዎቹ አልቀረበም፡፡

የተገኘውን ጥሬ ጨው አዮዳይዝድ አድርገው የሚያመርቱ ሁለት ፋብሪካዎች በአፋር ክልል የሚገኙ ሲሆን በመላው ሀገሪቱ 15 መጋዘኖች አሏቸው፡፡

እነዚህ ፋብሪካዎች ለአንድ ወር ያህል የገጠማቸውን ችግር ለንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ሆነ ለአፋር ክልል አለማሳወቃቸውን አቶ አስራት ገልጸዋል፡፡

በመጋዘኖቹ የነበረው ምርት ሲያልቅ ተጨማሪ ማቅረብ ስላልተቻለ ባለፉት ቀናት በነበረው የጨው ምርት ላይ ነጋዴው ዋጋ ጨምሮ ሲሸጥ ነበር ብለዋል፡፡

በአሁኑ ሰአት ጫኝ እና አውራጅ ሰራተኞች በኩንታል 15 ብር እንዲከፈላቸው የተስማሙ ሲሆን ከትላንት በስትያ በ40 ተሸከርካሪ ጨው ወደ ገበያ እንዲሰራጭ መደረጉን አቶ አስራት ተናግረዋል፡፡

ተጨማሪ ጨው የጫኑ 100 ተሸከርካሪዎች በመንገድ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡

ከፋብሪካዎቹ የተደረገ የዋጋ ጭማሪ ባይኖርም ምርቱ በሚገባ እስኪሰራጭ ድረስ ከ2 ብር ያልበለጠ ጭማሪ በአንድ ኪሎ ሊኖር እንደሚችል አቶ አስራት ጠቁመዋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *