አንዳንድ የህብረት ስራ ማህበራት በህገወጥ ግብይት በመሳተፍ የዋጋ ንረት እንዲከሰት እያደረጉ ነው ተባለ።

የህብረት ስራ ማህበራቱ ዋጋን የማረጋጋት ሚናን ይጫወታሉ ተብለው ቢጠብቁም የአንዳንድ የህብረት ስራ ማህበራት ድርጊት ከዚህ በተቃራኒ ሆኖ ተገኝቷል ነው የተባለው።

የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚንስቴር እንዳለው አንዳንድ የህብረት ስራ ማህበራት ያልተገባ ጥቅም ለማጋበስ የሰዓት እላፊን ተገን አድርገው ሸቀጦችን በህገወጥ መንገድ በውድ ዋጋ የሚሸጡ እንዳሉ አረጋግጫለሁ ብሏል ። በመሆኑም በዚህ ህገወጥ ድርጊት እየተሳተፉ ያሉ የህብረት ስራ ማህበራት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ሚንስቴሩ አስጠንቅቋል።

ከዚህ ባሻገርም ስግብግብ ነጋዴዎች እና እየተደረጉ ያሉ የኢኮኖሚ አሻጥሮች ለኑሮ ውድነቱ መጨመር በምክንያትነት ተነስተዋል።

አጥፊዎችን በመለየት ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ጀምሮ ሱቆችን እስከማሸግና ንግድ ፈቃድ እስከመሰረዝ የሚደርሱ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን የገለፀው ሚንስቴሩ ከፌደራል እስከ ወረዳ ድረስ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ እርምጃ የሚወስድ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱንም አስታውቋል ።

ግብር ሀይሉ ባደረገው ምልከታም ያለአግባብ የተከማቸ የዘይት ፣ የሩዝ ፣ የጨርቃጨርቅ እና የብረት ምርቶችን ይዞ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ማድረጉም ተነግሯል።

በ18 ቦታዎች ላይ ተከማችቶ የተገኘ ከ 1 ሺህ የጭነት መኪና በላይ ብረት በህጋዊ መንገድ ተሸጦ ገቢው ለመንግሥት እንዲሆን መወሰኑን የገለፀው ሚንስቴሩ ቂጥጥሩ በሌሎች ሸቀጦች ላይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል።

በሙሉቀን አሰፋ
ነሐሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *