በየአመቱ በከፍተኛ መጠን እያደገ የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛቱ ከአለም 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ተባለ፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በዛሬው እለት የስነ ህዝብ እና የአካባቢ ጥበቃ ድርጅት ከኮንሰርቲየም ኢትዮጵያ ጋር በጋራ በመተባበር የአለም ስነ ህዝብ ቀንን አክብረዋል፡፡

በፈረንጆቹ ከ1987 የአለም የህዝብ ብዛት 5 ቢሊየን የደረሰበትን ወቅት ምክንያት በማድረግ እስካሁን ድረስ እየተከበረ የሚገኝው የአለም ስነ ህዝብ በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ደረጃ ተከብሯል፡፡

በቦታው የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ባሁኑ ሰአት የአለም ህዝብ ብዛት 7 ነጥብ 8 ቢሊየን መድረሱን ተናግረዋል፡፡

የአለም የስነ ህዝብ ላይ ጥናቶች የሚያደርገው ፖፑላሽን ሪፈረንስ ቢሮ መረጃ መሰረት የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት 117 ሚሊየን መደረሱን ዶ/ር ሊያ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ በየ አመቱ የ2 ነጥብ 6 ሚሊየን እድገት እንደሚያሳይ ነው የተገለጸው፡፡

የኢትዮጵያ የስነ ህዝብ መጠን በዚህ አይነት መንገድ የሚቀጥል ከሆነ በ2035 ዓ.ም 160 ሚሊየን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በኢትዮጵያ የስነ ህዝብ እና የአካባቢ ጥበቃ ድርጅት የኮሚኒኬሽን ዳሬክተር ወ/ሮ ፍሬዘር ይህይስ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት በሀገር አቀፍ ደራጃ የስነ ህዝብ ፖሊሲ ጊዜው እንዳለፈበት ተናግረው ከሀገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ያገናዘበ አዲስ ፖሊሲ መቅረጽ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ቀኑን ማክበር የተፈለገው የስነ ህዝብ ጉዳይ የአንድ መስሪያ ቤት ጉዳይ ብቻ አለመሆኑን ለማሳወቅ እና የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ለማስገንዘብ እና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ ወ/ሮ ፍሬዘር ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

የውልደት ቁጥር በሚፈለገው መጠን አለመቀነስና የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በሚፈለገው መጠን ካለመዳረስ ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የሚገኘው የሀገራችን የህዝብ ቁጥር በአፍሪካ 2ኛና በዓለም ደግሞ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።

በሚቀጥሉት 30 ዓመታት የዓለም የህዝብ ቁጥር ዕድገት ከፍተኛውን ቁጥር ከሚይዙ ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ልትሆን እንደምትችል ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል
ነሃሴ 21 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *