ታሊባን አሜሪካ ከአፍጋኒታን ለቃ መውጣቷን ተከትሎ ‘ነፃ ሀገር’ ሲል አውጇል

ታሊባን የአሜሪካ ጦር ከ 20 ዓመታት ወረራ በኋላ መውጣቱን እንደ “ታሪካዊ ጊዜ” በመግለፅ አፍጋኒስታን “ነፃ እና ሉዓላዊ” ሀገር ናት ብሏል።

የመጨረሻው የአሜሪካ ወታደሮች ከሀገር ሲወጡ የታሊባን ተዋጊዎች ዛሬ የካቡልን አውሮፕላን ማረፊያ ተቆጣጥረዋል።

ይህንን አጋጣሚም ለማክበርም የካቡል ሰማይ ሌሊቱን በተኩስ እና በርችት ሲናወጥ አንግቷል እንደ አልጀዚራ ዘገባ፡፡

የታሊባኑ ቃል አቀባይ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ ከካቡል አውሮፕላን ማረፊያ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “የአፍጋኒስታን እስላማዊ ኢምሬት ነፃ እና ሉዓላዊ ሀገር እንደሆነ አንጠራጠርም።

“አሜሪካ ተሸነፈች… እናም አሁን በሀገራችን ስም ከሌላው ዓለም ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን እንፈልጋለን” ብለዋል።

ለአፍጋኒስታኖችም የታሊባን ሀይሎች “ነፃነታችንን እና እስላማዊ እሴቶቻችንን ይጠብቃሉ” በማለት ቃል ገብቷል።

የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ኃላፊ የሆኑት ማሪን ጄኔራል ፍራንክ ማኬንዚ ቀደም ሲል የአሜሪካ ወታደሮች ከካቡል እንደወጡ አስታውቀዋል።

“እኛ ለመውጣት የፈለግነውን ሰው ሁሉ አላወጣንም ግን እኔ እንደማስበው ሌላ 10 ቀናት ብንቆይ እኛ ለማውጣት የፈለግነውን ሁሉ እናስወጣ ነበር”ብለዋል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአሜሪካ ወታደሮችን ለቀው እንዲወጡ ነሐሴ 31 ቀን ቀነ ገደብ አስቀምጠዋል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።

ያይኔ አበባ ሻምበል
ነሐሴ 25 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.