አዲስ አበባ በህገ ወጥ እርድ ምክንያት በአመት 1.2 ቢሊዮን ብር ታጣለች

አዲስ አበባ በአመት በህገ ወጥ እርድ ምክንያት በአመት 1.2 ቢሊዮን ብር እንደምታጣ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የኢንፎርሜሽንና ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አታክልቲ ገብረሚካኤል ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

ለመጪውን የዘመን መለወጫ በአል የስጋ ውጤቶችን በጥራትና በተመጣጠነ ዋጋ ለማድረስ ዝግጅት መደረጉን ነግረውናል፡፡

በመሆኑም ድርጅቱ ለ2014 አዲስ ዓመት በአል ከ2 ሺህ 500 በላይ የዳልጋ ከብት እና ከ1 ሺ 500 በላይ በግና ፍየሎችን ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ድርጅቱ ለአንድ በሬ የእርድ አገልግሎት 867 ብር፣ ለፍየል እና ለበግ ደግሞ 120 ብር በማከፈል ቤት ድረስ ለማቅረብ እንደሚጠየቅ እና ለዚህም ከ40 በላይ ዘመናዊ የቄራ ተሽከርካሪዎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።

ለበዓሉ ህብረተሰቡ ከንጋቱ 11 ሰአት ጀምሮ ወደ ድርጅቱ በሬ፣ በግና ፍየል በማምጣት ከ30 እስከ 40 ደቂቃ ባለ ጊዜ አሳርዶ መውሰድ ይችላል ብለዋል።

ለቅርጫ የተዘጋጁም ካሉ በሬውን አምጥተው በማስመርመር የእርድ አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ ነው ያሉት።

ከእርድ በኋላ ድርጅቱ የሚፈለግበት ቦታ ድረስ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚያቀርብም ገልጸዋል።

በዋናው መስሪያ ቤት እና አቃቂ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ በሚገኙ ሱቆች በኪሎ የበግ ስጋ 210 ብር እንዲሁም የበሬ ስጋ በ285 ብር መግዛት እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ቄራዎች ደርጅት በቀን በአማካይ 3 ሺህ 500 ሰንጋዎችን በማረድ ለተጠቃሚዎች የማቅረብ አቅም አለው ሲሉ ሃላፊው ነግውናል።

በረድኤት ገበየሁ
ጳጉሜ 04 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *