ከሰሜን ወሎ ዞን የተፈናቀሉ ዜጎች የደሴ ከተማ ከሚያስተናግደዉ አቅም በላይ በመሆኑ ወደ ኮምቦልቻ እየተላኩ ነዉ ተባለ፡፡

ከሰሜን ወሎ ዞን በርካታ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች በደሴ እና ኮምቦልቻ መጠለላቸው ይታወቃል።

በአሁኑ ሰዓትም በደሴ ከተማ በመንግስትና በግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ዜጎች ቁጥር 275ሺህ መድረሱን የደሴ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ሰኢድ የሱፍ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።

ምክትል ከንቲባው እንዳሉት የተፈናቃዮች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ በመሆኑና ደሴ ከተማ ከዚህ በኋላ ተፈናቃዮችን መቀበል ስለማትችል ወደ ኮምቦልቻ እየላክናቸው ነው ብለዉናል።

ከተፈናቃይ ዜጎች ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣት አንጻር ደሴ ከተማ የቦታ እጥረት አጋጥሟልም ተብሏል።

ከሰሜን ወሎ የተፈናቀሉት 275ሺህ ዜጎች በመንግስት የተመዘገቡት ብቻ ናቸው ያሉት አቶ ሰኢድ፣ከቤተሰብ ጋር የተጠለሉት ቁጥር በዉል እንደማይታወቅና ቁጥሩ ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ከተፈናቃይ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞም የእርዳታ ተደራሽነት ችግር መኖሩን የተናገሩት ምክትል ከንቲባዉ፣እስካሁን ዩኒቨርሲቲዎች ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ግን ወደ አካባቢው እንዳልሄዱም አረጋግጠዉልናል።

በመቅደላዊት ደረጄ
መስከረም 04 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *