የልብ ቀዶ ጥገና ለማድረግ ከ7 ሺህ በላይ ህጻናት ወረፋ በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ ሰማን

በኢትዮጵያ የልብ ቀዶ ህክምና ለማድረግ ከ7ሺህ በላይ ህጻናት ወረፋ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን የሰማነው ከልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማእከል ነው፡፡

የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማእከል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ህሩይ አሊ በየአመቱ እስከ 500 የሚደርሱ ህጻናት የልብ ቀዶ ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ እና ቀዶ ህክምና የሚፈልጉ ህጻናት ቁጥር በየቀኑ እንደሚጨምር ኢትዮ ኤፍ ኤም ከሃላፊው ሰምቷል፡፡

ይህ ቁጥር ግን ካለው ወረፋ አንጻር ሲታይ በቂ አይደለም ብለዋል፡፡

በማእከሉ አላቂ እቃዎች በበቂ ሁኔታ ባለመኖራቸው የተነሳ ወረፋ የሚጠብቁ ህጻናት ህክምና እያገኙ አለመሆናቸውን እና መድሀኒትም ቢሆን በሚፈለገው መጠን አለመገኝቱ በስራው ላይ እንቅፋት እንደሆነበት ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

እንደ አላቂ እቃዎች እና መድሀኒቶች በበቂ መጠን ቢሟሉ ኖሮ ግን በአመት እስከ 1 ሺህ 500 ያህል ቀዶ ጥገና ማድረግ ይቻል እንደነበር አንስተዋል፡፡

“ወረፋ አስይዘው ቀዶ ህክምና ሊደረግላቸው ከማእከሉ ሲደወልላቸው ህይወታቸው እንዳለፈ የሚነገረን ጊዜ አለ” ፣ ይህ ሁኔታ ልብ የሚሰብር ነው” ሲሉ አቶ ህሩይ አሊ ተናግረዋል፡፡

ወረፋ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙትን ህጻናት ለመታደግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉ ሀላፊነት መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ድጋፍ ማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው 6710 ላይ ከአንድ ብር አንስቶ እስከ መቶ ብር ድረስ እገዛ ማድረግ ይችላል፡፡

የልብ ህመም አሁን ላይ በአለም ዋነኛ ገዳይ በሽታ እየሆነ መምጣቱን አለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያለመክቱ አቶ ህሩይ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ገልጸዋል፡፡

ሔኖክ ወ/ገብርኤል
መስከረም 19 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *