በቻይናዊያን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተሰራች መሳርያ አልባ ድሮን ያለ እረፍት ለረጅም ሰዓት የበረረች ድሮን በመባል የዓለም ክብረ ወሰንን ሰብራለች፡፡
ፌንግ አርዩ 3-100 የተሰኘችው ይህች በቤጂንግ የኤሮናቲክስ እና አስትሮናቲክስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተሰራች ድሮን ያለ ማቋረጥ ለ80 ሰዓት ከ46 ደቂቃ ከ35 ሴኮንድ በመብረር ነው ቀድሞ በቦይንግ ስር በሚተዳደረው ኦሪዮን በተሰኘ ተቋም በ80 ሰዓት፣ ከ2 ደቂቃ ከ52 ሴኮንድ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን ያሻሻለችው፡፡
የክንፍ ርዝማኔዋ 10 ሜትር የሆነው ድሮኗ በጋዝ ሞተር አማካኝነት የምትንቀሳቀስና ጠቅላላ ክብደቷም (የተሞላባትን ነዳጅ ጨምሮ) 60 ኪ.ግ ነው፡፡ ስያሜዋም የቻይና አቪዬሽን ኢንዱስትሪ አባት ከሚባሉት ከፌንግ ሩ የተወረሰ ነው፡፡
በረራው የተከናወነው ባሳለፍነው ግንቦት ወር በቻይና ሄናን ግዛት ውስጥ ነበር፡፡ ሆኖም ክብረ ወሰኑ ገና ባሳለፍነው እሁድ ነው በዓለም አቀፉ የኤሮናቲክስ ፌደሬሽን (FAI) እውቅና የተሰጠው፡፡
በበረራው ወቅት ድሮኗ በ300 ሜትር ከፍታ ላይ ስትጓዝ የነበረች ሲሆን በአየር ላይ እያለችም ምንም አይነት ተጨማሪ ነዳጅ እንዳይሞላላት ተከልክላ ነበር፡፡
እንደ ዩኒቨርሲቲው መረጃ ከሆነ ድሮኗን የሰራው የተማሪዎቹ ቡድን 25 ከተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የተውጣጡ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን ያቀፈ ነው፡፡ የተማሪዎቹ አማካኝ ዕድሜም ከ20 ዓመት በታች እንደሆነ ሺኑዋ ዘግቧል፡፡
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
መስከረም 26 ቀን 2014 ዓ.ም











