በመዋዕለ ህጻናት ግቢ ውስጥ በሚገኝ ትራንስፎርመር ምክንያት ስጋት እንደገባቸው የተማሪ ወላጆች ተናገሩ

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ እናት አጸደ ህጻናት ት/ቤት ግቢ ውስጥ በተተከለ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር የተነሳ የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ስጋት ላይ እንደወደቁ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።

መዋዕለ ህጻናቱ በ1989 ዓ.ም የተቋቋመ እንደሆነ እና የዛሬ 5 አመት ለመንገድ ስራ ሲባል የመዋዕለ ህጻናቱ የቅጥር ግቢ እንደፈረሰና በግቢው ውስጥ ለጊዜው በሚል ትራንስፎርመሩ እንዲተከል መደረጉን የትምህርት ቤቱ ባለቤት ነግረውናል።

ጣቢያችን በቦታው ተገኝቶ እንዳረጋገጠው ትራንስፎርመሩ ካሁን አሁን አደጋ ሊያደርስ ይችላል በማለት ትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን መገንዘብ ችለናል።

መምህራንም በግቢው ውስጥ ልጆችን ለማጫወት እየተሳቀቁ እንደሆነና አልፎ አልፎ የእሳት ብልጭታእና የፍንዳታ ድምጽ ስለሚወጣ አደጋ ሊከሰት ይችላል የሚል ፍርሀት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የትምህርት ቤቱ ባለቤት በተደጋጋሚ ትራንስፎርመሩ ከትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውጪ እንዲሆንላቸው ቢጠይቁም ለጥያቄያቸው መልስ የሚሰጣቸው አካል አለመገኘቱን በምሬት ገልጻዋል።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ሰሜን ሪጅን ዲስትሪክት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ገላን ተሊላ ጉዳዩን እንደሰሙ የጥናት ቡድን ልከው እንዴት ወደ ግቢው ሊተከል እንደቻለ አጣርተን ፣ ሀላፊነት የሚወስደው አካል ካጣሩ በኋላ ምላሽ እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል።

መቅደላዊት ደረጀ
ጥቅምት 17 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.