በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሃይሌ ጋርመንት አካባቢ በሚገኘዉ ሃና ማሪያም አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ምክንያቱ በውል ባልተገለፀ ሁኔታ ሆስፒታል ገብተው የነበሩ ተማሪዎች ትላንት ማምሻውን በደህና ሁኔታ ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ተነግሯል።
ወደ ቤተሰቦቻቸው በሰላም የተቀላቀሉት ተማሪዎች 153 እንደሆነ የጡሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል የኮሚኒኬሽን ዳሬክተር አቶ ይታያል አባተ ለኢትዮ ኤፍ ኤም አረጋግጠዋል።
ተማሪዎቹ ያጋጠማቸውን ሁኔታ ኢትዮ ኤፍ ኤም የሆስፒታሉን ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ሳምሶን ጉዱ የጠየቀ ሲሆን በሰዓቱ ተማሪዎቹ ለከፋ ጉዳት የሚዳርግ ነገር እንዳልገጠማቸው መግለጻቸው ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሀና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች የምግብ መመረዝ አጋጥሟቸዋል በሚል የሚሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ ነው ብሏል።
እርግጥ ተማሪዎቹ በትክክልም ያጋጠማቸው ምን ነበር ሲል ኢትዮ ኤፍ ኤም የጡሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል የኮሚኒኬሽን ዳሬክተር አቶ ይታያል አባተን የጠየቀ ሲሆን አሁን ላይ እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻለው የተማሪዎቹ ደህንነት እንጂ በርግጥም ተማሪዎቹ ምን እንዳጋጠማቸው ለማረጋገጥ አስፈላጊ ምርመራና መረጃ እንደሚያስፈልግ ነግረውናል፡፡
የውልሰው ገዝሙ
ጥቅምት 20 ቀን 2014 ዓ.ም











