23ኛው የጤና ጉባኤ በጅግጅጋ ከተማ መካሄድ ጀመረ

ምላሽ ሰጪ የጤና ስርዓት በአዲስ ምዕራፍ በሚል መሪ ቃል 23ኛው የጤና ጉባኤ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።

በጉባኤው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ኡስማን፣ ክልሉ አርብቶ አደር ማህበረሰብ የሚኖሩበትና ኋላ ቀር በመሆኑ በጤናው ዘርፍ ትልቅ ትኩረት ይፈልጋል ብለዋል።

የሶማሌ ክልል መንግስት የአርብቶ አደሩን የጤና ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ የጤና አገልግሎት ማስጀመሩንም አስታውቀዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፤ ልዩ ፍላጎት ለሚሹ አካባቢዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት በተለይም የህፃናትና የእናቶችን ጤና ከመጠበቅ አኳያ በአገር አቀፍ ደረጃ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የሥርዓተ ምግብን በተመለከተም ህፃናት የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ የሰቆጣ ቃል ኪዳን በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

የሰቆጣ ቃል ኪዳን መቶ 10 ሺህ ህፃናት ከመቀንጨር ችግር ማላቀቅ እንደቻለም ዶክተር ሊያ አንስተዋል።

የፌደራሉ መንግስት ከአጠቃላይ አመታዊ በጀቱ 13.3 በመቶ የሚሆነውን ለጤናው ዘርፍ ባለፈው አመት መመደቡም ታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪ የጤና ፋይናንስን ለማሳደግ በተሠራው ስራ 3መቶ 80ሚሊዮን ዶላር ከአጋር ተቋማት እንደተገኘም ሚኒስትሯ ገልፀዋል ።

የኮቪድ ወረርሽኝና ግጭቶች የጤናውን ዘርፍ ገቢ መሻማታቸውን የጤና ሚኒስትሯ አስታውቀዋል። በዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያቀደውን ዕቅድ እንዳያሳካ ችግር ፈጥሮበታል ተብሏል።

23ኛው የጤና ጉባኤ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የክልል የቢሮ ሃላፊዎች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና የአለም አቀፋ አጋር ተቋማት በመሣተፍ ላይ ናቸው።

አባቱ መረቀ
ጥቅምት 20 ቀን 2014

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *