ኢጋድ በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆም ሲጠይቅ የኬኒያና የኡጋንዳ ፕሬዝደንቶች በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ ያሉ ተፋላሚ ወገኖች ጦርነቱን በአስቸኳይ አቁመው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መስራት አለባቸው ሲል ኢጋድ ጠይቋል፡፡

ኢጋድ “ተፋላሚ ሀይሎቹ ፣ ውጥረቱን በማርገብ እና ልዩነቶቻቸውን በብሄራዊ ውይይትና ዕርቅ ለሀገርና ለአካባቢው በሚበጅ መልኩ እንዲፈቱ” አሳስቧል።

በሌላ በኩል የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ የምስራቅ አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ ግጭት ዙሪያ እንዲመክር መጠየቃቸው ተነግሯል፡፡

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በኢትዮጵያ ስላለው ግጭት ለመወያየት የምስራቅ አፍሪካ የመሪዎች ስብሰባን ለህዳር 16 ጠርተዋል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን ዛሬ መግለጻቸው ተዘግቧል።

“ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር እየተነጋገሩ ሲሆን ህውሓት ለመደራደር እና የተኩስ አቁም ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆኑ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል። ይህ ደግሞ ያሳስበናል“ ሲሉ የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ኦኬሎ ኦሪየም ለሮይተርስ ተናግረዋል።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ግጭቱን ለማስቆም ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ውይይት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ኡሁሩ ኬንያን ጨምሮ አፍሪካ እና ዓለም ሰላማዊ ኢትዮጵያን ማየት ይፈልጋል ያሉም ሲሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተመካክሮ ለአገሩ ሰላም መፍትሄ እንዲፈልግ አሳስበዋል፡፡

በሌላ ዜና የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፤ ፌልትማንን በቢሯቸው ተቀብለው በኢትዮጵያ እና ሱዳን ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን አስታውቀዋል፡፡

ያይኔአበባ ሻምበል
ጥቅምት 25 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.