የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት 3 ሺህ 898 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ማመንጨቱን በተቋሙ የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ሥራ አስፈፃሚ አስታወቁ፡፡

ሥራ አስፈፃሚው አቶ እያየሁ ሁንዴሳ እንደገለጹት በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 4 ሺህ 783 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ታቅዶ 3 ሺህ 898 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ማመንጨት ተችሏል፡፡

‹በበጀት ዓመቱ ማመንጨት ከተቻለው ውስጥ 3 ሺህ 778 ነጥብ 5 ጌጋ ዋት ሰዓት ከውሃ፣ 108 ነጥብ 4 ጌጋ ዋት ሰዓት ከንፋስ እንዲሁም 10 ነጥብ 7 ጊጋ ዋት ዋት ሰዓቱ ከደረቅ ቆሻሻ የመነጨ ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓት በስራ ላይ ከሚገኙት 21 የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ውስጥ ጢስ አባይ 2ኛ፣ ቆቃ፣ ጊቤ 3፣ አዋሽ 2ኛ እና 3ኛ እንዲሁም አዳማ 2 የኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያዎች ከታቀደላቸዉ በላይ ኃይል እንዳመነጩ ሥራ አስፈፃሚው ጠቁመዋል፡፡

የተሻለ ኃይል ማመንጨት በቻሉት ጣቢያዎች ይስተዋል የነበረው የመለዋወጫ ዕቃ አቅርቦት መፍትሄ በማግኘቱና በዩኒቶቻቸው ላይ የጥገና ስራ በመከናወኑ ጣቢያዎቹ በሙሉ አቅማቸው ኃይል በማመንጨት አፈጻፀማቸው ከዕቅድ በላይ እንዲሆን አስችሎታል፡፡

በአንፃሩ አመርቲ ነሼ፣ መልከ ዋከና፣ ጊቤ 1 እና 2፣ ፊንጫ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችና አዳማ 1 የንፋስ ማመንጫ ጣቢያ እንዲሁም ረጲ ከደረቅ ቆሻሻ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ያመነጫሉ ተብሎ ከታቀደላቸው በታች ካመነጩ ጣቢያዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

እንደ ቆቃ፣ አዋሽ 2ኛ እና 3ኛ ያሉ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ደግሞ ከመለዋወጫ አቅርቦት ጋር በተያያዘ አንዳንድ ዩኒቶቻቸው ለዓመታት ኃይል ማመንጨት አቁመው እንደነበር አቶ እያየሁ አስታውሰዋል፡፡

በሩብ ዓመቱ የግድቦች የውሃ አስተዳደር የተሻለ እንደነበር ያነሱት ሥራ አስፈፃሚው በሀገሪቱ ባለው ወቅታዊ ችግር ምክንያት የኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር መቀነሱና በሙሉ አቅም ኃይል ለማመንጨት እና ሠራተኞችን ከቦታ ቦታ በማዘዋወር ለማሰራት ፈተና እንደነበር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የላከልን መግላጫ ያመለክታል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ህዳር 15 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.