በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እየተመራ በሁሉም ግንባሮች ወደ ከፍተኛ የማጥቃት እንቅስቃሴ የገባው የ”ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” አስደናቂ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል ሲሉ የመንግስት ኮምንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ አስታውቀዋል።

በዚህም መሰረት በጋሸና ግንባር ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሀይል ሚሊሻና ፋኖ በጥምረት ባደረጉት ተጋድሎ የአርቢትን፣ የአቀትን፣ የዳቦና የጋሸና ከተሞችን ነጻ አውጥተዋል።

በዚህ ግምባር ጠላት ለበርካታ ወራት የዘረፈውን ሀብት በመጠቀም በወረራ የያዘውን አካባቢ ህዝብ በማስገደድ ያሰራውን ባለብዙ እርከን ኮንክሪት ምሽግ በተቀናጀ እቅድ፣ አመራርና ቴክኖሎጂ በመታገዝ በአነስተኛ መስዋዕትነት ምሽጉ ተሰብሯል።

በዚህ ግንባር በርካታ የነፍስ ወከፍና የቡድን ከባድ መሳሪያዎች በወገን ጦር ተማርከዋል።

ይህ ድል ለዝርፊያ የገባውን የጠላት ሀይል ወገቡን የቆረጠ ነው።

የወገን ጦር ጋሸናን መቆጣጠሩ ጠላት በላሊበላ፣ ወልዲያና ደሴ የተቆጣጠራቸውን አካባቢዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጽዳት መንገዱን ምቹ ያደርጋል።

የወገን ጦር የጋሸናን እና አካባቢውን ከመቆጣጠር አልፎ በላሊባለ፣ ወልዲያና ወገል ጤና አቅጣጫ በአሁኑ ሰአት ወደፊት እየገሰገሰ ይገኛል።

በወረኢሉ ግንባር የጃማደጎሎ ወረኢሉ ገነቴ፣ ፊንጮፍቱ፣ አቀስታ ከተሞች በጀግኖቹ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሀይ ሚሊሻና ፋኖ ጥምረት ከአሸባሪው ነጻ ወጥተዋል።

በሸዋ ግንባር የመዘዞ፣ ሞላሌ፣ ሸዋሮቢትና አካባቢው እንዲሁም ራሳና አካባቢው ጀግኖቹ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሀይል ሚሊሻና ፋኖ በጥምረት ባደረጉት ተጋድሎ ከአሸባሪው ህወሓት ነጻ ወጥተዋል። ጅግኖቹ ወደፊት እየገሰገሱም ይገኛሉ።

በምስራቅ ግንባር በጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአፋር ልዩ ሀይልና ሚሊሻ ባደረጉት ተጋድሎ ነጻ የወጡት የካሳጊታ፣ ቡርቃ ዋኢማ ጪፍቱ ድሬሩቃ፣ ጭፍራ አለሌ ሱሉላ ከተሞች ሙሉ በሙሉ ከጠላት ጸድተዋል፤ የአካባቢው አስተዳደር ወደ ቦታው ተመልሷል ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ገልጿል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ህዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *