ፀረ ሰላም ኃይሎች በሱዳን ድንበር ሰርገው ለመግባት ያደረጉት ሙከራ ከሸፈ

ከኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ተልዕኮ ተቀብለው በድንበር አካባቢ ሰርጎ ለመግባት በሞከሩ የአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ እንዲሁም የቤህነን ታጣቂዎች በጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና በክልሉ ፀጥታ ኃይሎች የጋራ ጥምረት ርምጃ እንደተወሰደባቸው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የታጣቂዎቹ ተልዕኮ የህዳሴ ግድብ ተገንብቶ ስራ ላይ እንዳይውል እና መንግስት የያዘው የብልፅግና ጉዞ እንዳይሳካ ለማደናቀፍ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አብዱልአዚም መሀመድ ገልፀዋል።

በተወሰደው ርምጃም ፀረ ሰላም ኃይሎቹ ይጠቀምባቸው የነበሩ በርካታ ጥይቶች እና ፈንጂዎች እንዲሁም አርፒጂ፣ ሞርታር እና ሌሎች ልዩ ልዩ ከባድ መሳሪያዎች መማረካቸውን ኮሚሽነሩ አክለው ገልጸዋል።

የክልሉን ሰላምን በዘላቂነት ለማስቀጠል በተከናወነው ኦፕሬሽን ህብረተሰቡም ከፍተኛ ሚና እንደነበረው የጠቀሱት ኮሚሽነሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስተግበር የፀጥታ ስራው ከአጎራባች ክልሎች ጋር የጋራ ጥምረት በመፍጠር በእቅድ እየተመራ ተጠናክሮ መቀሉን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል አሸባሪው ህወሓት እና ተላላኪው ሸኔ ሀገርን ለማፈራረስ የወጠኑት ሴራ መክሸፉን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል አራርሳ መርዳሳ ገለፁ፡፡

ባለፉት ጊዜያት በሀገሪቱ ብሎም በክልሉ ጠላት ሀገር ለማፈራረስ ጥረት አድርጓል፣ ብዙ ጥፋቶችን አጥፍቷል ያሉት ኮሚሽነሩ ይህንን ለመቀልበስ መላው ህብረተሰብ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የክልሉ የፀጥታ ኃይል ከሌሎች የፀጥታ አካላት እና ከማህበረሰቡ ጋር ባደረገው ቅንጅት በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የሸኔ ቡድን ላይ አስፈላጊውን እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽነሩ አክለውም ለአሸባሪው ሸኔ አገልግሎት ሊውሉ የነበሩ በርካታ የጦር መስሪያዎች ከመያዝ እና ቡድኑ የጦር ግብዓቶችን እንዳያገኝ የግንኙነት መረቡን ከመበጣጠስ አኳያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለፀጥታ ኃይሉ ተጨማሪ አቅም እና ጉልበት እንደሆነው መግለፃቸውን ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ህዳር 27 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *