ቡና ባንክ የ9 ኛው ዙር የ “ይቀበሉ፣ይሸለሙ“ እድለኞች ሽልማቶች አስረከበ

በቡና ባንክ ከውጪ የሚላኩ ገንዘባቸውን በባንኩ የመነዘሩ 31 ለሚሆኑ ባለ እድለኞች የደረሳቸውን ሽልማቶች ዛሬ ተበርክቶላቸዋል።

በዚሁ መርሃ ግብር የ2020 ሞዴል ሱዙኪ ዲዛየር ዘመናዊ የቤት አውቶሞቢል፣ ዘመናዊ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖችን እንዲሁም ፍሪጆችና ሌሎች ዘመናዊ መገልገያ ቁሳቁሶችን እጣው ለወጣለቸው ሰዎች ርክክብ ተደርጓል።

የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ዳይሬክተር አቶ ጠና ኃ/ማሪያም በርክክብ መርሀግብሩ ወቅት እንዳሉት፣ የውጭ ምንዛሬ ይቀበሉ፣ ይመንዝሩ፣ ይሸለሙ መርሃግብር፣ በህጋዊ መንገድ የሚካሄድ የውጭ ምንዛሬን በማሳደግ፣ ሀገሪቱ ልታገኝ የምትችላቸውን ጥቅሞች ለማበረታታት ባንኩ ከሚሰራቸው ስራዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በዚህ ወቅት የምእራባዊያን መንግስታት በሚያደርጓቸው ኢ-ፍትሃዊ ውሳኔዎች በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድሩት ጫና በኢኮኖሚያችን ላይ የደረሰውን ጉዳት ተቋቁመን ለመሻገር በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵውያን የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ለገና በዓል ወደ ሀገር ቤት ሲገቡ ገንዘባቸውን በህጋዊ መንገድ በባንክ እንዲመነዝሩም ጥሪ አቅርበዋል።

የውጭ ሀገር ገንዘቦችን በባንክ ስርዓት መመንዘር ባህል እንዲሆን ለማድረግ ባንኩ እነዚህን የማበረታች ሽልማቶችን ጨምሮ የተለያዩ አማራጮችን እንደሚያቀርብ አቶ ጠና ጠቁመዋል።

ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ከተመሰረተ 12 አመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በአዲስ አበባና በመላው ኢትዮጵያ ወደ 329 ቅርንጫፎችን በመክፈት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ባንክ ነው።

ጅብሪል መሀመድ
ታህሳስ 14 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *