” እስከ ትላንት ድረስ ከ 121 ዲያስፖራዎች የህክምና ቁሳቁሶች ተረክበናል ” የጤና ሚኒስቴር

የጠቅላይ ሚኒስተሩን ጥሪ ተቀብለው ከተለያዩ ሃገራትየተለያዩ ድጋፎችን ይዘው ወደ ኢትዮጲያ እየገቡ ነው፡፡

ከድጋፎቹም መካከል የተለያዩ መድሀኒቶችና የህክምና መስጫ መሳሪያዎችን እስከ ትላንት 19 /2014 ደረስ ከ 121 ዲያስፖራዎች መረከባቸውን በጤና ሚኒስቴር የመድሃኒት እና የህክምና መሳርያዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ረጋሳ ባይሳ ለኢቲዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

እርሳቸው እንዳሉት ከሆነ የተለያዩ ዲያስፖራዎች እየገቡ መሆኑን ተከትሎ ድጋፍን ለማስረከብ ገና ከሚመጡበት ሃገር ሳይነሱ ጀምሮ በጤና ሚኒስቴር በተከፈቱት አራት የኢሜል አድራሻዎች አማካኝነት ምዝገባ ሲያደርጉ ነበር ብለውናል፡፡

የሚያመጡት የህክምና የግብአት አይነት ተለይቶ ከታወቀ እና ማረጋገጫ ከተሰጣቸው በኋላ እዚህ ሲደርሱ የተሰጣቸውን ማረጋገጫ በማሳየት የርክክብ ስራው የሚከናወን መሆኑን አንስተዋል፡፡

ይህ ሂደት ሲያልቅ ደግሞ ላመጡት እቃ ደረሰኝ ተቀብለው የእውቅና ፣ የምስጋና ሰርተፍኬት እየተሰጠ ነው ያለው ሲሉ ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

የሚሰጠውን ደረሰኝ የግድ መቀበላቸው የሚያስፈልገው መንግስት ያመጡትን እቃ እና እነርሱን አውቅና ሊሰጥ ስለሚገባ ነው ብለዋል፡፡

በርክክብ ስርዓቱ ላይ መጉላላት እንዳይኖር 11 ሰዎች 24 ሰዓት ለዚህ አገልግሎት ቦሌ አየር መንገድ ተመድበው እየሰሩ መሆኑን አንስተው
ፍጥነቱ ላይ ለሚነሳው ጥያቄም አቶ ረጋሳ ምላሽ ሲሰጡ አንዳንድ ጊዜ የቦታ አለመገጣጠም እና የተለያዩ መውጫ በሮች እንደመኖራቸው ቦታውን ቶሎ ባለማግኘት መዘግየት ሊኖር ይችላል ብለዋል ፡፡

በቦሌ ኤርፖርት ይሄንን አገልግሎት እያስተባበረ የሚገኘው የመድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ፣ የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ፣ በጤና ሚኒስቴር ውስጥ የተቋቋመው ግብረ ሃይል ይገኝበታል ብለዋል ፡፡

ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም

ረድኤት ገበየሁ

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *