“ከየትኛውም በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ቡድን ጋር ለመደራደር የታቀደ ምንም ነገር የለም ” የህግ ፍትህ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ዙሪያ ሰአታትን የወሰደ ውይይት ካካሄደ በኋላ በአብላጫ የአባላቱ ድጋፍ አጽድቋል፡፡

የዚህ ምክክር ኮሚሽን መቋቋም እንደሚናፈሰው ወሬ ከየትኛውም በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ቡድን ጋር ለመደራደር የታቀደ አለመሆኑ ከግንዛቤ ሊገባ እንደሚገባም በምክርቤቱ የህግ ፍትህ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ገልፀዋል፡፡

በረቁቁ ዙሪያ የመከሩት የምክር ቤቱ አባላት ፣ ኮሚሽን ቀደም ብሎ መቋቋም እንደነበረበበት ባነሷቸው ነጥቦች ላይ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡

በአንፃሩ ጉዳዩ የጥድፊያ እንዳይሆን በስክነት እና በእርጋታ ሁሉን አሳታፊ በሆነ መልኩ ተመክሮበት ቢፀድቅ ይሻላል ሲሉም ሃሳባቸውን ያቀረቡ አባላት ነበሩ፡፡

ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክርቤቱን የተቀላቀሉ አባላት የተሸለ እድል እና ሃሳባቸውን እንዲያንፀባርቁ የተመቻቹ መድረኮች መኖራቸውን አመስግነው አሁንም ቢሆን ምክክሩ የኢትዮጲያ ህዝብ አንድ አካል የሆነው የትግራይ ህዝብ በአሸባሪው ቡድን እየተጨቆነ እና አማራጭ የሌለበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ሳለ የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን ነገር ምክርቤቱ እንዲለይም ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም በምክርቤቱ የኮሚሽኑ መቋቋም ለሃገራዊ አንድነት እና መግባባት ያለው ፋይዳ በአጠቃላይ አባላቱ ተመሳሳይ አረዳድ ቢኖራቸውም በአንፃሩ በአፋር እና በአማራ ክልል በጦርነቱ ሳቢያ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቦታቸው ሳይመለሱ እና ካሉበት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የስነልቦናዊ ቀውስ ሳያገግሙ በምን መልኩ በዚህ ጉዳይ እንዲመክሩ እንደሚደረግም በጥያቄ መልክ አንስተውታል፡፡

በዛሬው የምክርቤቱ 6ኛውን የ1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ ልዩ ስብሰባው የኢትዮጲያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽንን አዋጅ ቁጥር 1265/2014 እንዲሆን በአብላጫ ድምፅ በ13 ተቃውሞ እና በአንድ ድምፀታ እቅቦ አፅድቆታል፡፡

ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም

አብድልሰላም አንሳር

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.