በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚነሱ ግጭቶች፣የንብረት ውድመቶችና ማፈናቀሎች፣የኮሮና ወረርሽኝ፣ የአንበጣ መንጋ፣ ድርቅ አጎንብሶ ቀና ማለት ያቃተውን ኢኮኖሚያችንን ይበልጥ እንዲጎብጥ ከተጫኑት ምክንያቶች መካከል ናቸው፡፡
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነና ከጥቅምት 2013 ጀምሮ ደግሞ ጦርነት ታከለበት፡፡ ይህ ጦርነት በጦርነትነቱ ካወደመው በተጨማሪ አበዳሪዎችና ረጂዎች ለጠላት ዕቅፍ ለሀገራችን ጀርባ በመስጠታቸው ምክንያት ይቺውም ኢኮኖሚ ማዕቀብ እንድታስተናግድ ሆኗል፡፡
የሰሜኑ ጦርነት ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ምን ያህል ጥልቀት አለው የሚለውን በቁጥር ታግዞ ለመናገር ጠለቅ ያለ ጥናት እንደሚፈልግ ኢትዮ ኤፍ ኤም ያናገራቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የተናገሩ ሲሆን ከስብራቱ ልናገግም የምንችልባቸውን አማራጮችንም ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ዲፓርትመንት ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ ፤ የዋጋ ንረት፣ የውጪ ምንዛሬ ዕጥረት፣ የወደመውን መልሶ መገንባት የሚያስፈልግ ከፍተኛ ወጪ፣ የጦር ሀይሉን ይዞ ለመቆየት የሚጠይቀው ወጪ፤ ፤በጦርነቱ ምክንያት የምናሰተናግዳቸው አራት ከፊታችን የተቀደኑ ከባባድ ፈተናዎች ናቸው ብለዋል::
ከጦርነት በኋላ ካፒታሊስት ሀገራት እንኳን ከጦርነት በኋላ ገበያ ላይ ጣልቃ ይገባሉ የሚሉት ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ መንግስት መሰረታዊ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ቁጥጥር ማድረግ አለበት ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በአመት በአማካይ በእርዳታ የምናገኘው 1.5 ቢሊዮን ዶላርና ሸጠን የምናገኘው 3 ቢሊዮን ዶላር ተደምሮ እንኳን ዘመዶቻችን ከውጪ የሚልኩልን 5 እና 6 ቢሊዮን ዶላር ይበልጣል የሚሉት ፕሮፌሰር አለማየሁ በውጪ የሚኖሩ ዘመዶቻችን የሚልኩልንን ገንዘብ በህጋዊ መንገድ እንዲልኩልን ለማድረግ፤ በነሱ አርበኝነት ላይ ብቻ መታመን ሳይሆን አማራጭ ማበረታቻዎችን ማቅረብ አለብን ብለዋል፡፡
በህገ ወጥ ካለው የምንዛሬ ዋጋ ቀንሶ ከህጋዊው የምንዛሬ ዋጋ ደግሞ ከፍ አድርጎ ዲያስፖራው በህጋዊ መንገድ እንዲልክ የተለየ የምንዛሬ ዋጋ መስጠትን እንደ አንድ አማራጭ አቅርበዋል፡፡
እንደ ፐሮፌሰር አለማየሁ፤ ከዚህ ቀደም ከጦርነት በኋላ መንግስታት ወጪ ሲበዛባቸው ብር በብዛት በማተማቸው ምክንያት የዋጋ ንረቱንና ግሽበቱን በከፍተኛ ሁኔታ አባብሰዋል፤ የኛ መንግስት ከዚያ በመማር፤ ቦንድ በማዘጋጀት ከህዝቡ ገንዘብ መሰብሰብ አለበት ብለዋል፡፡
ለትናንሽ ለመካከለኛና ለትላልቅ ድርጅቶች ፤እንደ የአቅማቸው ሶስት አይነት ቦንድ ተዘጋጅቶ፤ ከአመት ትርፋቸው ላይ ቢገዙ ጥሩ ይሆናል ሲሉ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
በፕሮፌሰር አለማየሁ ባነሷቸው ሀሳቦች የሚስማሙት ሌላው የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ ሙሼ ሰሙ ፤ እንደውም በውጪ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ብቻ የሚሆን ቦንድ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
ሰዎች በእርዳታ ገንዘብ ስጡ ሲባሉና ነገ የምንመልስላችሁን ገንዘብ በቦንድ መልክ አበድሩን ሲባሉ ገንዘብ ለማውጣት የሚኖራቸው ተነሳሽነት የተለያየ ነው ያሉ ሲሆን ለእርዳታ ሲባል 100 ዶላር የሚሰጠው ዲያስፖራ ነገ በሚመለስልህ ዶላር ቦንድ ግዛ ሲባል 10 ሺህ ዶላር ሊያወጣ ይችላል ብለዋል፡፡
ትልልቅ ገንዘብ ሊገኝ ስለሚችል በቦንድ አማካይነት የውጪ ምንዛሬ ላይ የሚፈጠርብንን ችግር ያቀልልናል የሚሉት አቶ ሙሼ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን በውጪ ለሚኖሩ ቱርካውያን ያቀረቡት ጥሪ በአንድ ወር 1 ቢሊዮን ዶላር ማስገኘቱን አስታውሰዋል፡፡
በመንግስት ቤት የተለመደው የገንዘብ ዝርክርክነት እና የሀብት ብክነትም ካልቆመ፣ ሌብነቱና የጥፋት እጁም መሰብሰብ ካልቻለ ፤ ከደረሰብን የኢኮኖሚ ድቀት ማገገም አንችልም ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል አቶ ሙሼ፡፡
ከዚህ በኋላ ጦርነቱ ምን ያህል ይቆያል የሚለውን በእርግጠኝነት አለማወቃችን ከዚህ በኋላ ምን ውድመት ኢኮኖሚው እንደሚጠብቀው እርግጠኛ እንዳንሆን ያደርገናል የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹ የተከሰተው ህልቆ መሳፍርት ችግር ነውና ከዚህ ማጥ ለመውጣት ረዘም ያለ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም ብለዋል፡፡
ሔኖክ አስራት
ታህሳስ 27 ቀን 2014 ዓ.ም











