በኬንያ በሀገር አቀፍ ደረጃ መብራት በመቋረጡ ምክንያት የታሰሩት ሶስቱ የኤሌክትሪክ ሀይል መስሪያ ቤት ከፍተኛ ሀላፊዎች ክስ ተመሰረተባቸው

ሀላፊዎቹ ግዴታቸውን ዘንግተዋል በማለት ፖሊስ ምርመራ ጀምሯል ሆን ተብሎ በተፈፀመ ጥፋትና ዳተኝነት ምክንያት በዚህ ወር መጀመርያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ኤሌክትሪክ በመቋረጡ ፤ ለኬንያ የኤሌክትሪክ ሀይል የሚያከፋፍለው የመንግስት መስሪያ ቤት ከፍተኛ ሀላፊዎች ላይ ክሱ እንደተመሰረተ ከፍርድ ቤት የተገኘው ሰነድ ያሳያል፡፡

በመላ ምስራቅ አፍሪካ መብራት አጠፋህ ተብሎ ተከሶ የሚያውቅ የለም የሚሉት የተከሳሾቹ ጠበቃ በምስራቅ አፍሪካ በመብራት መጥፋት ምክንያት ክስ የተመሰረተባቸው የመጀመርያዎቹ ደንበኞቼ ናቸው ብለዋል፡፡

እንደ አውሮፓውያኑ ጥር 11 2022 ከፍተኛ ቮልት ኤሌክትሪክ ወደ መዲናዋ ናይሮቢ የሚያስተላልፈው መስመር በመበላሸቱ ምክንያት የኬንያ መኖርያ ቤቶችና የቢዝነስ ተቋማት ለበርካታ ሰአታት በጨለማ ተውጠው ነበር፡፡

የኤሌክትሪክ ሀይል የሚያቀርበው ተቋሙ፣ ከፍተኛ ቮልት የሚያስተላለፉት መስመሮችን የሚሸከሙት ምሶሶዎች በመውደቃቸው ምክንያት ነው ኤሌክትሪክ የተቋረጠው ይበል እንጂ ፖሊስ ከፍተኛ ሀላፊዎች ግዴታቸውን ባለመወጣታቸው ነው ምሶሶዎቹ የወደቁት ብሎ ምርመራ ጀምሯል፡፡

የአቃቤ ህግ የክስ ወረቀት እንደሚያሳየውም ሶስቱ ከፍተኛ ሀላፊዎች በዳተኝነት ሆን ብለው የሰሩት ጥፋት ነው የሚል ሲሆን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ቮልት የሚያስተላልፉትን መስመሮች የሚሸከሙትን ምሶሶዎች ባለመጠበቃቸውና ባለመጠገናቸው ኬንያን ለኪሳራ የዳረገ ሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ መቋረጥ አጋጥሟል ይላል፡፡

ኤሌክትሪኩ ከመቋረጡ ከሳምንት በፊት ምሶሶዎቹ እንደወደቁ ማህብረሰቡ ጥቆማ ቢያደርስም እርምጃ መውሰድ ሳይችሉ ቀርተዋል በሚልም ሀላፊዎቹ ተከሰዋል፡፡

ሶስቱም ከፍተኛ ሀላፊዎች ክሱን መካዳቸውን የዘገበው ሰንዴይ ታይምስ በ 1 ሚሊዮን ሽልንግ ዋስ እንደተለቀቁና ለሚቀጥለው ወር መጨረሻም መቀጠራቸውን በዘገባው ጠቅሷል፡፡

ባለፈው ሳምንት የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እንደ ኤሌክትሪክ ሀይል ማሰራጫ ያሉ መሰረተ ልማቶችን የሚያበላሹ ሰዎችን እየያዝን ነው ያሉ ሲሆን እንደዚህ ኢኮኖሚውን የሚያወድም አጥፊ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት በሀገር ክህደት መከሰስ አለባቸው ብለው ነበር፡፡

ሔኖክ አስራት
ጥር 19 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *