ኢትዮጵያ ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት የሚኖራት የውጭ ምንዛሬ ቢበዛ የሁለት ወር ብቻ እንደሆነ የተነገረው የምእራባዊያን ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያ ጉዳዮች እና ድህረ ግጭት ላይ ጥናታዊ ፅሑፍ በቀረበበት መድረክ ላይ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ በዚሁ መድረክ ላይ እንደተናገሩት ባሁኑ ሰአት ኢትዮጵያ ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት ያላት የውጭ ምንዛሬ ክምችት ቢበዛ ለሁለት ወር የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
የምዕራባዊያን ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያ ጉዳዮች እና ድህረ ግጭት ላይ ባተኮረው ጥናታዊ ጽሁፋቸው ፕሮፌሰሩ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት አንጻር ሲታይ ኢትዮጵያ በእጇ ላይ ያለው የውጭ ምንዛሬ በጣም ውስን ነው ብለዋል፡፡
ለምሳሌ ያህልም እንደ ኬኒያ ያሉ ሀገራት ለስድስት ወር የሚሆን የውጭ ምንዛሬ ክምችት እንዳላቸውም ነው ምሁሩ የተናገሩት፡፡
የውጭ ምንዛሬው ዕጥረቱ በጦርነቱ እና በምእራባዊያን ትጽእኖ ምክንያት ሊከሰት መቻሉን ምሁሩ ተናግረዋል፡፡
በጦርነቱ እና በምእራባዊያን ትጽእኖ ምክንያት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ሊቀንስ ስለሚችል እንዲሁም እርዳታ የሚሰጡ ሀገራትም ድጋፋቸውን የሚያቋርጡ ከሆነ በከፍተኛ ሁኔታ ጫና የሚኖረው በውጭ ምንዛሬው ላይ ነው ብለዋል ፕሮፌሰር አለማየሁ፡፡
ሔኖክ ወ/ገብርኤል
ጥር 18 ቀን 2014 ዓ.ም











