የኢ.ፌ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር ሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነዶችን በማዘጋጀትና በመገልገል በጉምሩክ ኮሚሽን የተወረሰ ንብረትን በማውጣት ለግል ጥቅም ያዋሉ ሁለት ግለሰቦች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቷል፡፡
እንደ ዐቃቤ ህግ ክስ ሰይድ ፋንታው አሊ እና ጥላሁን አበጋዝ ሁን የተባሉ ተከሳሾች የሙስና ወንጀል አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23(1)(ሀ) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ አንዳርጋቸው ብስራት በተባለ አስመጪ ስም ወደ ሀገር ገብቶ ከቃሊቲ ወደብ መውጣት ባለበት ተገቢ ጊዜ ባለመውጣቱ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የተወረሰ ብዛቱ 89 ካርቶን አጠቃላይ የዋጋ ግምቱ ብር 1,538,392.81 የሆነ የመኪና መለዋወጫ (ኩሽኔት) ከሚገኝበት ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ቃሊቲ ቅ/ጽ/ቤት ትክክለኛ የአሰራር ሂደቶችን ተከትሎ የወጣ በማስመሰል ለዚህም እንዲረዳቸው በተለያዩ ግለሰቦች ስም ሀሰተኛ ሰነዶችን ማለትም ካሊድ አህመድ በሚል ስም የተዘጋጀ ሀሰተኛ የተሸከርካሪ መግቢያ ፍቃድ ቁጥር 08353፣ አሊ ሀምዛ በሚል ስም የተዘጋጀ ሀሰተኛ የጉምሩክ መልቀቅያ ደረሰኝ ቁጥር CA000589120 እንዲሁም ዛኪር ሙሳ በሚል ስም በቀን15/03/14 ዓ/ም የተዘጋጀ ሀሰተኛ የኢትዮጵያ ባህር ሎጅስቲክስ የሰርቪስ ክፍያ ሰነድ በማዘጋጀትና እቃውን በማውጣትና ለግል ጥቅማቸው በማዋል ወንጀል ተጠርጥረዋል ፡፡
የክስ መዝገቡ በዝርዝር እንደሚያስረዳዉ 1ኛ ተከሳሽ ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም እቃዎቹን በኮንቴነር ወስጥ አድርጎ በከባድ ተሸከርካሪ አስጭኖ ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን ቃሊቲ ቅርንጫፍ ይዞ ከወጣ በኋላ በአንደኛ የዐቃቤ ህግ ምስክር አማካኝነት ለሁለተኛ ተከሳሽ በመላክ፣ 2ኛ ተከሰሽ በበኩሉ በቀን 16/03/2014 በአንደኛ ተከሳሽ አማካኝነት ከጉምሩክ የወጣውን የመኪና መለዋወጫ ትክክለኛ የንብረቱ ባለቤት ሳይሆን መስሎ የተቀበለ እና ለዚሁ ጉዳይ በተከራየው መጋዘን ውስጥ እንዲራገፍ ካደረገ በኋላ የወንጀሉን ፍንጭ ለማጥፋት በማሰብ ዕቃዉ የተጫነበትን ኮንቴነር ፍቃዱ ይትባረክ ለተባለ ግለሰብ የሸጠለት በመሆኑ ሁለቱም ተከሳሾች በፈፀሙት ሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነዶች በማዘጋጀትና በመገልገል በጉምሩክ ኮሚሽን የተወረሰ ንብረትን በማውጣት ለግል ጥቅም ማዋል የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
በመሆኑም ተከሳሾቹ ጥር 17/2014 ዓ/ም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሙስና ወንጀከል ችሎት የቀረቡ ሲሆን የቀረበባቸው ክስ እና ማስረጃ በችሎት ተነቦላቸው የክስ መቃወሚያ ያላቸው እንደሆነ ከጥር 26/2014 በፊት እንዲያቀርቡ እና ዐቃቤ ህግ ምላሽ እንዲሰጥ ትዕዛዝ የተሰጠ ሲሆን ፍርድ ቤቱም በሚቀርበው መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ለጥር 26/2014 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ጥር 19 ቀን 2014 ዓ.ም











