ሩሲያ ዩክሬንን በሚቀጥለው ወር ልትወር እንደምትችል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተናገሩ

በሚቀጥለው ወር ሩሲያ ዩክሬንን የምትወርበት ዕድል ሰፊ ነው ብላለች አሜሪካ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትናንት ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌኒስኪ ጋር በስልክ በነበራቸው ቆይታ ፤ በየካቲት ዩክሬን በሩሲያ ልትወረር ትችላለች ማለታቸውን የነጩ ቤተ መንግስት ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ገልፀዋል፡፡

ስለዚህ ጉዳይ ለወራት ስናስጠነቅቅ ከርመናል ብለዋል የነጩ ቤተ መንግስት ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባዩ ኤምሊ ሆርኔ

ፕሬዝዳንት ባይደን ፤አሜሪካ ከአጋሮቿ ጋር በመሆን ለሩሲያ ወረራ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነች ብለዋል፡፡

ሩሲያ በበኩሏ ፤ ፍላጎቶቻችንን አሜሪካ ውድቅ አድርጋለች፤ ስለዚህ ቀውሱ ሊፈታ የሚችልበት ዕድል ጠባብ ነው እያለች ሲሆን ከፍላጎቶቻችን ዋነኛው ደግሞ ዩክሬን ወደ ኔቶ ለመቀላቀል የምታደርገውን ጥረት ታቁም የሚለው ነው ብላለች፡፡

ምዕራባውያን ደግሞ አንዲት ሉአላዊት ሀገር የፈለገችውን ማህበር ለመቀላቀል ሌላ ሀገር ማስፈቀድ የለባትም ፤ መብቷ ነው እያሉ ነው፡፡

ሩሲያ 100 ሺህ ወታደሮቿን ዩክሬን ድንበር ላይ ማስፈሯ ወረራ ልትፈፅም ነው የሚል ፍራቻ ቀስቅሷል፡፡

በግዛቴ ውስጥ የፈለኩትን ማድረግ እችላለሁ የምትለው ሩሲያ ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ ነው ጦሩን በቦታው ያሰፈርኩት እያለች ነው፡፡

ምዕራባውያን ሩሲያ ዩክሬንን የምትወር ከሆነ በጦር ከመግጠም ጎን ለጎን ኢኮኖሚዋን በማዕቀብ እናሽመደምዳለን እያሉ ነው፡፡

አሜሪካ ከሩሲያ ወደ ምዕራብ አውሮፓ ነዳጅ የሚወስደውን 1 ሺህ 225 ኪ.ሜ የሚረዝመውን ቱቦ እንደምታስቆመውም ዝታለች፡፡
ቢቢሲ

ሔኖክ አስራት
ጥር 20 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *