በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የወጡ የኮቪድ 19 መከላከያ መንገዶችን በማያከብሩ አሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለው ቅጣት ዳግም ተግባራዊ መደረግ ጀምረ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ እንዳስታወቀው የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ በትራንስፖርት ዘርፍ የተቀመጠውን መመሪያ ተግባራዊ በማያደርጉ አሽከርካሪዎች ላይ ከዛሬ ጀምሮ ቁጥጥር እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት የተሽከርካሪዎችን ንጽህና መጠበቅ፣ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች ማስክ መጠቀም እንዲሁም ማስክ ያላደረጉ ተሳፋሪዎች አገልግሎት እንዳያገኙ ማድረግ እንደሚገባም መመሪያ ተላልፏል፡፡

የኮቪድ ስርጭት ለመግታት በወጣው መመሪያ መሰረት ማስክ ያላደረጉ አሽከርካሪዎች እና ረዳቶች ከተገኙ ብር 1 ሺህ የሚቀጡ ሲሆን ማስክ ያላደረጉ ተሳፋሪ በሚጭኑበት ወቅት በአንድ ሰው 500 ብር የሚያስቀጣ ይሆናል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የአዲስ አበባ ትራንስፓርት ቢሮ መግለጫ የሰጠ ሲሆን በመግለጫ ወቅት የትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ይርጋለም ብርሃኔ እንደተናገሩት በትራንስፖርት ዘርፍ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት አስገዳጅ መመሪያዎችን በማውጣት ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

አቶ ይርጋለም አክለውም በአሁኑ ወቅት በነዋሪዎች ዘንድ የጥንቃቄ መርሆዎች እየተዘነጉ በመምጣቸው የስርጭት መጠኑ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የስርጭት መጠኑ ለመቀነስ ትራንስፖርት በምንገለገልበት ወቅት ማስክ ማድረግና ሌሎች ህጎች አስገዳጅ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በትራንስፖርት ዘርፍ በከተማዋ የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመግታት የወጣውን መመሪያ በማይተገብሩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ምክትል ቢሮ ኃላፊው አሳስበዋል፡፡

የውልሰው ገዝሙ
ጥር 20 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *