በደሴ ከተማ 17.1 ቢሊየን ብር የሚገመት ዘረፋና ውድመት መድረሱ ተነግሯል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በአሸባሪው ቡድን በተጎዱት የሰሜን ሸዋ፣ የደቡብ ወሎ እና የሰሜን ወሎ ከተሞች የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡

የደሴ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ ገ/መስቀል እንዳሉት በከተማዋ 17.1 ቢሊየን ብር የሚገመት ዘረፋና ውድመት ድርሷል፡፡

ከንቲባው የፌደራል እና የክልል መንግስታት እንዲሁም የተለያዩ ለጋሾች አበረታች ድጋፍ እያደረጉ ቢሆንም የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ቋሚ ኮሚቴው ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

ለሀገራዊ ለውጡ ስኬት የደሴ ከተማ ህዝብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው የከተማዋ ነዋሪዎች በነበረው ውይይት ተናግረዋል፡፡

የአሽባሪው የህወሃት ቡድን በአከባቢው ላይ አረመኔያዊ ድርጊት መፈጸሙንም አንስተዋል፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች፤ አንገታቸውን ከመድፋት ይልቅ በመልሶ ማቋቋሙ እየተረባረቡ ስለመሆናቸው ለቋሚ ኮሚቴው አባላት አስረድተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) ችግሩ አገራዊ እንደሆነ ሁሉ አገራዊ መፍትሄ እንደሚያስፈልገው ጠቁመው፤ አከባቢው ከቀድሞ በተሻለ እንዲቋቋም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እንሰራለን ብለዋል።

ቋሚ ኮሚቴው የመልሶ ማቋቋሙን ሂደት ለመከታተልና ለመደገፍ ከአማራ ክልል አመራሮች ጋር እንደሚወያይ፤ በቀጣይ ደግሞ በአፋር ክልል ተመሳሳይ ምልከታ እንሚያደርግ ከቋሚ ኮሚቴው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ጥር 23 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.