ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት ስድስት ወራት 10.1 ሚሊዮን ደንበኞችን አፍርቻለሁ አለ

ዛሬ የ2014 በጀት አመት የመጀመሪያ መንፈቅ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ት ፍሬህይወት ታምሩ ለመገናኛ ብዙሀን አቅርበዋል፡፡

ወ/ት ፍሬህይወት ባለፉት ስድስት ወራት የኩባንያው እቅዶች በአመዛኙ ሙሉ በሙሉ የተሳኩ ቢሆንም በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ምክንያት መቶ በመቶ አፈጻጸም ያልተመዘገበባቸው እቅዶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

የደንበኞች ቁጥር 60.8 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ20 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ተጨማሪ 10.1 ሚሊዮን ደንበኞች ማፍራት ተችሏል፡፡

በሪፖርቱ የገመድ አልባ ተጠቃሚዎች ቁጥር 58.7 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን የመደበኛ ብሮድባንድ ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር 443 ሺ የደረሰ ሲሆን የ43 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

133 ሺ አዲስ የመደበኛ ብሮድባንድ ኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ባለፉት ስድስት ወራት ማፍራት መቻሉን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አስታውቀዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ኩባንያው 28 ቢሊዮን ብር ገቢ ያገኘ ሲሆን የእቅዱን 86.4 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡

ኩባንያው በውጭ ምንዛሬ ገቢ ከሚያገኝባቸው አገልግሎቶች 74.8 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያገኘ ሲሆን የእቅዱን 89.3 ማሳካት መቻሉ ተገልጿል፡፡

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራ እና አፋር ክልል መስፋፋቱ በተጨማሪም በኮቪድ 19 አለም አቀፋዊ ተጽእኖ ምክንያት ከውጭ የሚመጡ ግብአቶች እና ቁሳቁሶች በወቅቱ መግባት አለመቻላቸው ኩባንያው ከገቢ አንጻር በስድስት ወራት ውስጥ ለማግኘት ያቀደውን ያህል እንዳያሳካ ያደረጉ ምክንያቶች መሆናቸውን ወ/ት ፍሬህይወት አስታውቀዋል፡፡

መንግሥታዊው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኢትዮ ቴሌኮም፣ በአጠቃላይ ካሉት 8 ሺ የሞባይል ጣቢያዎች መካከል 3 ሺ 473 የሚሆኑት በጦርነቱ ምክንያት አገልግሎት አለመስጠታቸውን አብራርተዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በዛሬው መግለጫቸው ኢትዮ ቴሌኮም በ2014 በጀት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት 28 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታውቀዋል፡፡

ሆኖም ተቋሙ ያገኘው ገቢ በዕቅድ ከያዘው 86 ነጥብ 4 በመቶውን ያሳካ መሆኑን ፍሬሕይወት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በዕቅድ ያስቀመጠውን ያህል ገቢ ማግኘት ያልቻለው በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ምክንያት እንደሆነ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አመልክተዋል።

ለዚህ በማሳያነት በሚል ተቋሙ ካሉት ስምንት ሺህ የሞባይል ጣቢያዎች ውስጥ 3 ሺ 473 ያህሉ በጦርነቱ ምክንያት አገልግሎት አለመስጠታቸውን ነው ያነሱት፡፡

ሔኖክ ወ/ገብርኤል
ጥር 23 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *