ድንገት በተደረገ ፍተሻ ካዘጋጁት ሀሰተኛ መታወቂያ እና ደረሰኞች ጋር ተይዘው በዐቃቤ ህግ ክስ የተመሰረተባቸው ስምንት ተከሳሾች በእስራት እና በገንዘብ እንዲቀጡ ተወሰነ።


በሀሰተኛ መታወቂያ የንግድ ፍቃድ አውጥተው ሀሰተኛ ደረሰኞችን ለማዘጋጀትና ለማተም የሚያገለግሉ ማሽኖችን በመጠቀም ወንጀሎችን ሲፈፅሙ የተያዙ ስምንት ተከሳሾች ከ12 ዓመት እስከ ፅኑ እስራት ድረስ በሚደርስ ቅጣት እንዲቀጡ ተወሰነባቸው።

በአዲስ አበባ ከተማ በየካ ክፍለ ከተማ በ2011 ሀሰተኛ መታወቂያ አዘጋጅተው የንግድ ፍቃድ በማውጣት፣ ሀሰተኛ ደረሰኞችን በመያዝና ለሽያጭ በማመቻቸት፣ ምንም አይነት ህጋዊ ግብይት ሳይፈፀም ደረሰኝ በመስጠትና በመቀበል፣ ስራ ላይ ተሰማርተው እያለ ድንገት በተደረገ ፍተሻ ተይዞባቸዋል፡፡

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 9ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ተጠይቀው በዐቃቤ ህግ ክስ ላይ በተጠቀሰው መሰረት የወንጀል ድርጊቱን ሙሉ በሙሉ ባለማመናቸው እንደ ክህደት ተቆጥሮ ዐቃቤ ህግ ተከሳሾች ወንጀሉን ስለመፈፀማቸው የሚያስረዱ 9 የምስክሮች ቃል እንዲሁም ተከሳሾች በተለያዩ ጊዜያት ወንጀል ለመስራት የተጠቀሙባቸው ሀሰተኛ ሰነዶችና ማሽኖችን በኢግዚቪትነት አቅርቦ ድርጊቱ በተከሳሾች መፈፀሙን በበቂ ሁኔታ አስረድቷል፡፡

ተከሳሾችም ይህንኑ ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው ችሎቱ የጥፋተኝነት ፍርድ በመስጠት ተከሳሾች እንደተመሰረተባቸው ክስና እንደ ወንጀል ተሳትፏቸው፤ 1ኛ- አላዛር ገዘህኝ የተባለው ተከሳሽ በ12 ዓመት ፅኑ እስራትና በ60 ሺህ ብር ፣ 2ኛ መንግስትአብ ሀይሉ እና አበባው ወርቅነህ የተባሉ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ8 ዓመት ከ5 ወር ፅኑ እስራትና በ125 ሺህ ብር፤ 3ኛ – አብርሃም አቤ የተባለው ተከሳሽ በ6 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት 4ኛ ተከሳሽ ረሃሙ ሙሉጌታ የተባለው ተከሳሽ በ5 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራትና በ50 ሺህ ብር ፤ እና እንዲሁም 5ኛ ይሁንላቸው አሊ የተባለው ተከሳሽ በ5 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራትና በ45 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ እንደተወሰነባቸዋል ከፍትህ ሚንስቴር ማህበራዊ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ጥር 24 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *