ከአስርት አመታት ወዲህ ከፍተኛ የሆነ ድርቅ በሀገራችን መከሰቱን መንግስት አሳወቀ፡፡

ከአስርት አመታት ወዲህ ሀገራችን አይታ የማታውቀው ከፍተኛ የሆነ ድርቅ መከሰቱን መንግስት አሳውቋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ በአካባቢዎቹ በሚኖሩ ዜጎች ላይ ሊደርስ የሚችለውን የሰብአዊ ጉዳት ለመቀነስ መንግስት ከአጋር አካላት ጋር ጠንካራ ስራ እየሰራ ስለመሆኑ ተነስቷል፡፡

በሶማሌ ክልል ባሉ ሰባት ዞኖች ድርቅ መከሰቱን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጸዋል፡፡

በዚህም ወደ 960 ሺህ ሰዎች የእለት ደራሽ እርዳታ እየቀረበላቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡

በአካባቢው ቀደም ባለው ጊዜ የዕለት ደራሽ እርዳታ ከሚደረግላቸው ዜጎች ጋር ሲደመርም አሁን ቁጥሩ ወደ 3.3 ሚሊየን ደርሷል ነው ያሉት፡፡

ይህ ስራ በመንግስት ጥረት ብቻ የሚሰራ እንዳልሆነ የተናገሩት ወ/ሮ ሰላማዊት አጋር ተቋማትም እየተሳተፉ ስለመሆናቸውም ገልጸዋል፡፡

በተለይ ደግሞ የአለም የምግብ ፕሮግራም ከለጋሾች ባገኘው ወደ 255 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት በአካባቢው ላይ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት ማደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ሌላው ጉዳት የገጠመው የኦሮሚያ ክልል ሲሆን በተለይ ደግሞ የቦረና ዞን ለድርቅ አደጋ ተጋላጭ የሆኑት ከ166 ሺህ በላይ ዜጎች መለየታቸውን እና ወደ እለት ደራሽ እርዳታ እንዲገቡ ተደርጓል ያሉ ሲሆን ከዚህ ቀደም ከነበረው የተረጂዎች ቁጥር ጋር ሲደመር 426 ሺ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

ከሀምሌ ጀምሮ እስከ ታህሳስ ወር ድረስ ባሉት ስድስት ወራት በተለይ በአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በኩል 69 ሺ ኩንታል ድጋፍ መቅረቡንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል፡፡

ከ41 ሺ ኩንታል በላይ መሰራጨቱን አስታውቀው ቀሪውም በመጓጓዝ ላይ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በተመሳሳይም 251 ሺህ የምስራቅ ባሌ የድርቅ ተጎጂዎች 42 ሺ ኩንታል መመደቡን እና እየተጓጓዘ እንደሆነም አንስተዋል፡፡

እንዲሁም የደቡብ ክልል የኦሞ ዞን ላሉ 77 ሺ ዜጎች 11 ሺ ኩንታል እህል ተልኳል ብለዋል፡፡

ወደ ትግራይ ክልልም መሰረታዊ ድጋፎችን ከ41 በላይ የደርሶ መልስ በረራዎችን መደረጋቸውን አሳውቀዋል፡፡

በክልሉ ከ50 በላይ አጋር አካላት እገዛ እያደረጉ ነው ካሉ በኃላ ከጥቂት ቀናት በፊት 43 አስቸኳይ እርዳታ የጫኑ የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች በአፋር በኩል ህውሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት መመለሳቸውን አንስተዋል፡፡

ያይኔአበባ ሻምበል
ጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.