የኦቨርማርስ አሳዛኝ መጨረሻ …

ማርክ ኦቨርማርስ በአያክስ የእግር ኳሳዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል ፡፡ የሆላንዱ ክለብ ‹‹ ለሴት የሙያ ባልደረቦቹ በርካታ ተገቢ ያልሆኑ መልዕክቶችን ልኳል ›› ብሎ ከወነጀለው በኋላ ኦቨርማርስ ራሱን ከሃላፊነቱ አንስቷል ፡፡
አያክስ ባወጣው መግለጫ የቀድሞው የአርሰናል እና ባርሴሎና የመስመር ተጫዋች ‹‹ወዲያውኑ ስራውን ይለቅቃል›› ብሏል ፡፡

የ48 ዓመቱ ኦቨርማርስ ከ2012 ጀምሮ በሃላፊነቱ የቆየ ሲሆን በቅርቡ እስከ 2026 ሰኔ በሃላፊነቱ የሚያቆየው ኮንትራት መፈራረሙ ይታወሳል፡፡

ኦቨርማርስ በድርጊቱ ‹‹ማፈሩን ›› እና የፈጸመው ነገር ‹‹ተቀባይነት የሌለው›› መሆኑን ተናግሯል ፡፡

‹‹መስመር እንዳለፍኩ አልተገነዘብኩም ነበር ፤ ባለፉት ቀናት ግን የፈጸምኩት ነገር ተገቢ አለመሆኑ ግልጽ ተደርጎልኛል ይቅርታም እጠይቃለሁ ›› ብሏል ፡፡
ኦቨርማርስ ከ 1992 እስከ 1997 ድርስ በአያክስ ማሊያ 130 ጨዋታዎችን አከናውኗል ፤ ሶስት የኤሬዲቪዚዬ ዋንጫዎችን አንስቷል፤ የሆላንድ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ እና ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊም ሆኗል ፡፡

በ1997 አርሰናልን ተቀላቀለ፤ ከመድፈኞቹ ጋር የፕሪምየር ሊግ እና የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫ አነሳ፡፡

የቀድሞ የቡድን ጓደኛው እና የአያክስ የወቅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤድዊን ቫን ደር ሳር ‹‹ ሁሉንም የሚያግባባ ውሳኔ አሳልፈናል ›› ብሏል፡፡

‹‹ የስራ ባልደረቦቼን የማገዝ ሃላፊነት አለብኝ፤ ደህንነቱ የተጠበቀ ስፖርት እና የስራ ከባቢ ያስፈልጋል፡፡ ወደፊት መሰል አጋጣሚዎች እንዳይከሰቱ ጠንክረን እንሰራለን ›› ብሏል፡፡

አያክስ ከ21 ጨዋታዎች በኋላ በኤሬዲቪዚዬ ከአናት ተቀምጧል፡፡

አቤል ጀቤሳ
ጥር 30 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *