በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ባለሀብቶች ብድር ከመስጠት አንስቶ ሌሎችም ድጋፎች ያገኛሉ ተባለ፡፡

በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ባለሃብቶች የክልሉ መንግስት አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጣቸው የተገለፀ ሲሆን በቂ ብድር እንዲያገኙ የሚያስችል ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው፡፡

የአማራ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሀላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት በክልሉ በተለያየ ዘርፍ ኢንቨስት በማድረግ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በአሸባሪው የህውሀት ሀይል ውድመት የደረሰባቸው ባለሀብቶችን ለመደገፍ መንግስት ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡

ጉዳት የደረሰባቸው ባለሀብቶች በህግ ማስከበር ወቅት ገንዘብ ከመስጠት አንስቶ እስከ ግንባር ድረስ በመዝመት ወገንተኝነታቸውን ያስመሰከሩ ነበሩ ሲሉ ነው አቶ ግዛቸው የተናገሩት፡፡

በመሆኑም ባለሀብቶቹ ወደ ቀድሞ ስራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ ለማመቻቸት የክልሉ መንግስት ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ፋብሪካዎች ኢንዱስትሪዎች ሆቴሎች እና ሌሎችም የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱ ይታወቃል፡፡

ሔኖክ ወ/ገብርኤል
የካቲት 02 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.