ቅዳሜ እና እሁድ በአዲስ አበባ ከተማ በደረሰ ሶስት ድንገተኛ የእሳት አደጋዎች አራት ሰዎች የመቁሰል አደጋ ሲደርስባቸው በንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል፡፡
አንደኛ የእሳት አደጋ የደረሰው በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት ሂርቱ ሞጆ ተብሎ በሚጠራው የጥብቅ ደን ውስጥ ነው፡፡
የአደጋው ምክንያት ደግሞ ለቆሻሻ ተብሎ የተለኮሰ እሳት እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
የእሳት እና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግኑኝነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደገለፁት በአደጋው 200 ሺህ ብር የሚደርስ ንብረት ሙሉ በሙሉ ለውድመት ተዳርጓል ብለዋል፡፡
ሌላኛው አደጋ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ጎማ ተራ አካባቢ በሚገኝ አንድ አነስተኛ ሆቴል ቤት ሲሆን በዚህ አደጋ ምክንያት 300 ሺህ ብር የሚጠጋ ንብረት መውድሙ አቶ ንጋቱ ተናግረዋል፡፡
እንደዚሁም 10ሚሊየን ብር የሚጠጋ ንብረት ደግሞ ማዳን ተችሏልም ብለዋል፡፡
ሌላኛው አደጋ የእሳት አደጋ የደረሰው ደግሞ በጉለሌ ክፍለ ከተማ በእፅዋት ማእከል ሲሆን የአደጋው አይነትም የሰደድ እሳት ነው፡፡
በዚህኛው የእሳት አደጋ የተነሳም 10ሺህ ብር የሚደርስ ንብረት ለውድመት ተዳርጓል ብለዋል፡፡
እንደዚሁም 10ሚሊየን ብር የሚጠጋ ንብረት ከአደጋው መታደግ እንደተቻለ የእሳት እና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግኑኝነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለጣቢያችን ገልፀዋል፡፡
ሔኖክ ወ/ገብርኤል
የካቲት 07 ቀን 2014 ዓ.ም











