አሸዋ ሶሉሽን ቴክኖሎጂ አክሲዮን ማህበር የ7 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት አስጀመረ፡፡

አሸዋ ሶሉሽን ቴክኖሎጂ አክሲዮን ማህበር በዛሬው እለት ስራ ለሁሉ የተሰኘ የ7 ሚሊዮን ብር ፕሮጅክት መጀመሩን የአክሲዮን ማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል በቀለ ተናግረዋል፡፡

ይህ ፕሮጀክት ይፋ የሆነው በቀነኒሳ ሆቴል ሲሆን በዋናነት የኢንተርኔት ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለገበያ የሚውሉ ምርቶችን ማቅረብ እንደሆነና ፤በቅድሚያ 500 ፍላጎቱ ያላቸው የኢንተርኔት ተጠቃሚ ወጣቶችን፤ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪዎ ችን እና በኢንተርኔት ገበያ ላይ የተሰማሩ ሻጮችን ተሳታፊ የሚያደርግ እድል ይዞ መምጣቱን ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ እንደመነሻ በአዲስ አበባ ከተማ ተግባራዊ እንደሚሆን የተናገሩት አቶ ዳንኤል፤ በቀጣይ ጊዜያት ወደ ክልል ከተሞች ለማስፋት እቅድ መያዛቸውን ገልፀዋል፡፡

አክሲዮን ማህበሩ አላማ አድርጎ የተነሳባቸውን ፕሮጀክቶችን ለማሳካት፤ለሽያጭ ካቀረበው 200 ሚሊዮን ብር የአክሲዮን መካከል ግማሽ ያህሉን መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፤ የታቀደው ሙሉ የአክሲዮን ሽያጭ ከተጠናቀቀ በኋላ 160 ሚሊዮኑን ለኢ-ኮሜርስ፤20 ሚሊዮን ለሎጅስቲክ፤10 ሚሊዮን ለኢ-ዋሌት የገንዘብ ዝውውር እና 10 ሚሊዮኑን ደግሞ በኢንተርኔት አማካኝነት የትምህርት አገልግሎትን ለማስኬድ ይውላል ነው የተባለው፡፡

ከሁለት አመት በፊት የተጀመረው የአሸዋ ሶሉሽን ቴክኖሎጂ አክሲዮን ማህበር፤ በቀጣይ 10 ዓመታት በርካታ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት ያቀደ ሲሆን፤ በነዚህ አመታት ውስጥ ለ5 ሚሊየን ህዝብ የስራ እድል የመፍጠር አላማንም ይዞ እየሰራ መሆኑን አቶ ዳንኤል በቀለ ተናግረዋል፡፡

መሳይ ገ/መድህን
የካቲት 08 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.