በድንገት በተነሳ የእሳት አደጋ 7 ሚሊየን ብር የተገመተ ንብረት ወደመ።

በአዲስ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታዉ ኮልፌ እፎይታ ገበያ አካባቢ የካቲት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 4:21 ላይ በተነሳ እሳት 7 ሚሊየን ብር የተገመተ ንብረት ሲወድም በሁለት የእሳት አደጋ ሰራተኞች ላይ በጭስ መታፈን ጉዳት እንደደረሰባቸው ኢትዮ ኤፍ ኤም ሰምቷል።

የእሳትና የአደጋ ስጋት ኮምሽን 13 የእሳት ማጥፊያ ተሽከርካሪዎች ከ87 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ጋር በቦታዉ እንዲደርስ በማድረጉ እሳቱ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉን የኮምሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።

እሳቱን መቆጣጠር በመቻሉም 50 ሚሊየን ብር የተገመተ ንብረት ማዳን ተችሏል ብለውናል።

የንግድ ሱቆቹ በቀላሉ ሊቀጣጠሉ ከሚችሉ ከቆርቆሮ እና ከእንጨት መሰራታቸዉም እንዲሁም የኤሌክትሪክ መስመር ፈጥኖ አለመቋረጡና የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች መግቢያ መንገድ አለመኖር ለእሳት አደጋዉ መባባስ አስተዋጾ ማድረጉንም ነግረውናል።

ኮልፌ አጠና ተራ የሚገኙ የገበያ ማእከላት ተደጋጋሚ የእሳት አደጋ ከሚያጋጥማቸዉ ገበያ ማእከላት አንዱ ነዉ።

በሌላ በኩል የካቲት 21 እና 22 በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታዉ በተለምዶ ለምለም ጀርባ በሚገኝ ተቆፍሮ ክፍቱን በተተወና ዉሀ ባቆረ ጉድጓድ ውስጥ እድሜዉ 32 የተገመተ ግለሰብ ህይወቱ አልፎ ተገኝቷል።

እንዲሁም አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ልዩ ቦታዉ ግዮን ጋዝ ጀርባ በሚገኝ ወንዝ ዉስጥ አድሜዉ 35 የሆነ ሰዉ ህይወቱ አልፎ መገኘቱንም አቶ ንጋቱ ነግረውናል።

የድንገተኛ አደጋ ጠላቂ ዋናተኞቻችን አስከሬን አዉጥተዉ ለተጨማሪ ምርመራ ለፖሊስ አስረክበዋል።

የውልሰው ገዝሙ
የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *