በጦርነት ወቅት የሸሹ የብልፅግና አመራሮች ወደ ስልጣናቸው ተመልሰው እያስተዳደሩ በመሆኑ ህዝቡ ለፍተኛ ቀውስ ተዳርጓል፡- ኢዜማ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከጦርነት በኋላ በጦርነቱ ወደ ተጎዱ አካባቢዎች ልዑካን በመላክ ቅኝት ማድረጉን ገልጧል፡፡

በጦርነት ወቅት የሸሹ የብልፅግና አመራሮች ወደ ክልሉ ተመልሰው ማስተዳደር ከጀመሩ በኋላ ህዝቡን ለከፍተኛ ቀውስ መዳረጋቸው ሳያንስ እነሱ የድል አጥቢያ አርበኛ ሆነው ሲታገል የነበረውን ህዝብ ከወያኔ ጋር እጅና ጓንት ሆናችሁ ስትሰሩ ነበር በሚል እየፈረጁትና እየወነጀሉት ነው ብሏል ፓርቲው፡፡

በተለይ በአማራ ክልል ደሴ፣ ኮምቦልቻና ወልዲያ በጦርነቱ ወቅት የሸሹ አመራሮች ጦርነቱ ካለቀ በኋላ ተመልሰው ስልጣን መያዛቸው ሳያንስ ለምግብ እርዳታ ስርጭት በሕዝቡ የተወከሉ ኮሚቴዎችን ባለሥልጣኖቹ በራሳቸው ጊዜ ሸኝተው እርዳታውን በአግባቡ እንዳይደርስ አድርገው ለግል ጥቅማቸው እያዋሉት ይገኛሉ ሲል ኢዜማ ገልጧል፡፡

በጦርነት ወቅት የሸሹ የብልፅግና አመራሮች ወደ ክልሉ ተመልሰው ማስተዳደር ከጀመሩ በኋላ በርካታ አዳዲስ የታጠቁ ቡድኖችና ሃይማኖት ተኮር ወጣት ሊጎችን የመሳሰሉ አደረጃጀቶች እየተፈጠሩ እንደሆነ የገለፀው ፓርቲው በአማራ ክልል ህገ ወጥ የጦር መሳርያ ሽያጭና ዝውውር የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል ብሏል፡፡

በህዝብ የተጠሉና በሕወሓት የአገዛዝ ወቅቶች ለሕወሓት አጎብዳጅ የነበሩ ካድሬዎች ዛሬም የስልጣን ማማው ላይ ተቀምጠው እንደሚገኙና ሌሎችም እጅግ አሳሳቢና አስቸኳይ መፍትሄ የሚሹ ችገሮች በክልሉ እንደታዘበ ፓርቲው ገልጧል፡፡

የኢዜማ ዋና ፀሐፊ አቶ አበበ አካሉ፤ ጦርነቱ በተካሄደባቸው የአማራ ክልል አካባቢዊች ያለውን ሙስና፤ አስክሬን መሸጥ ነው የቀረው ሲሉ ገልፀውታል፡፡

መጋዘን ውስጥ የነበረውን እህል ለወራሪው ጥለው ህዝብን አስርበው ፤ የራሳቸውን ነገር አመቻችተው ሸሽተው ስለወጡ ወራሪው ሀይል ህዝቡም ላይ ንብረቱም ላይ እንደፈለገ ሊፈነጭ ችሏል ብለዋል፡፡

ኮምቦልቻ ላይ የተዘረፈው ንብረት የአመራሩ ንዝህላልነትና ከህውሀት ጋር በማበር የተካሄደ እንደሆነ የተናገሩት አቶ አበበ ባንክ ያለ ገንዘብና ውድ ቁሳቁሶች እንዲወጡ ስናሳስብ አመራሮቹ ፍቃደኛ አልነበሩም ብለዋል፡፡

የኦነግሸኔን ጥቃት የሚያስቆም አካል ሊገኝ አለመቻሉ የተመለከተ መግለጫ ኢዜማ ያወጣ ሲሆን በሀገሪቱ የሚከሰቱ ግጭት መነሻዎች በመንግሥታዊ መዋቅር የታገዙ ናቸው ሲል ኢዜማ ገልጧል፡፡

ከመነሻቸው እስከ መድረሻቸው መዋቅራዊ ድጋፍ ያላቸው ወንጀሎቹና ግጭቶቹ ከዕለት ወደ ዕለት መጠናቸው እየበዛ አፈጻጸማቸውም እየረቀቀ እንደመጣ የገለፁት ደግሞ የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ የሸዋስ አሰፋ ሲሆኑ ህዝቡ ሲያልቅ ቆመው እንደማያዩ ተናግረዋል፡፡

ሔኖክ አስራት
የካቲት 28 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *