ብዙ ጊዜ ኮንቲነር ለመጠበቅ ከሚጠፋው ጊዜ ባሻገር መርከብ ላይ የሚቆይበት ጊዜ ሲጨምር ያለው ቅጣት አስመጪዎች ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረባቸዉ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡
የኢትዮ ሎጀስቲክስ የዘርፍ ማህበራት ፕሬዝዳንት የሆኑት ወ/ሮ ኤልሳቤት ጌታሁን ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት፣ ችግሩ በቴክኒካል ኮሚቴ መጠናቱን ተናግረው በአመዛኙ የጅቡቲ እና የኢትዮጲያ ኮሪደር መካከል ያለው የስራ ሰዓት አለመገጣጠም መሆኑን አንስተዋል።
እርሳቸው እንዳሉት የስራ ሰዓት አለመገጣጠም ማለት የጅቡቲ ቢሮዎች የሚከፈቱበት ሰዓት ለምሳሌ ከጠዋት 2 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት ሲሰሩ ከሰዓት ደግሞ 10 ሰዓት ገብተው ምሽት አንድ ሰዓት ይወጣሉ፡፡
በኢትዮጵያ ደግሞ ጠዋት 2፡30 ገብተው እስከ 6፡30 ከሰዓት ደግሞ 7፡30 እስከ 11፡30 ነው የሚሰሩት ይህ ከሰኞ እስከ ሃሙስ ያለው የስራ ጊዜን ብቻ የሚሸፍን መሆኑን ተናግረው አርብ እና ቅዳሜን የጅቡቲ አብዛኛው መስርያ ቤቶች እንደማይሰሩ ተነግሯል፡፡
በተጨማረም እሁድ ደግሞ በኢትዮጵያ በኩል ወደ ስራ የማይገባበት ጊዜ መሆኑን ነው ወ/ሮ ኤልሳ የገለፁት ፡፡
በተያያዘም በሳምንት 40 ሰዓት የስራ ጊዜ ቢኖርም 20 ሰዓቱ በመሸዋወድ እንደሚያልፍ ተናግረዋል።
ወ/ሮ ኤልሳቤት እንዳሉት፣ተፅዕኖውን ለማቃለል በጅቢቲ በኩልም ሆነ በኢትዮጲያ በኩል ያለውን የስራ ሰዓት ለማሻሻል እና የስራ ቀናቶችን ተመሳሳይ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በተደጋጋሚ አስመጪዎች የጅቡቲ ወደብ ላይ እቃዎች ተከማችተው ቀን እየቆጠሩ ለተጨማሪ ክፍያ እንደሚዳረጉ የሚነሳ ሲሆን ይህ አሰራር ተግባራዊ ሲደረግ የተሻለ ትርፍ እና ቅልጥፍና እንደሚኖረው ወ/ሮ ኤልሳቤት ጨምረው ተናግረዋል።
በረድኤት ገበየሁ
የካቲት 28 ቀን 2014 ዓ.ም











