“መሰረተ ልማቶች ሳይሟሉ ቤቶችን እንድንረከብ መገደዳችን ቅሬታ ፈጥሮብናል “ሲሉ የጋራ መኖሪያ ቤት ባለእድለኞች ተናገሩ፡፡

በ13ተኛው ዙር የኮዬ ፈጬ የጋራ መኖሪያ ቤት ባለእድለኞች እንድንረከብ የተገደድነው ቤት ውሃ፣ መብራት እና ሽንት ቤትን የመሰሉ መሰረተ ልማቶች ሳይሟሉለት መሆኑ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለውሃ ብቻ በጄሪካን 30 ብር እንደሚከፍሉ ተናግረው፤ ይህም በሳምንት ውስጥ ከ500 እስከ 1ሺ ብር እንደሚያወጡ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል፡፡

ነዋሪዎቹ የሽንት ቤት መስመር ዝርጋታ ባለመጠናቀቁ እና የባኞ ቤት እቃዎች ባለመቅረባቸው ሽንት ቤት ቆፍረው እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል፡፡

ይህ ደግሞ ህጻናት እና አቅመ ደካማዎች ስላሉ እነሱን ሽንት ቤት ለማስጠቀም እስከማዘል ደርሰናል ያሉ ሲሆን የግንባታ ጥራት ችግሩ በራሱ ስጋት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል ፡፡

የኤሌክትሪክ መስመር ባለመዘርጋቱ ለግንባታ ስራ የተዘጋጀውን ቆጣሪ መጠቀም ትችላላቹ ብንባልም ቆጣሪው ከኛ በጣም የራቀ በመሆኑ የኤሌክትሪክ ገመድ ለመዘርጋት ለከፍተኛ ወጪ ተዳርገናል ሲሉ ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት የኮዬ ፈጬ የጋራ መኖሪያ ቤት ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ሃብተ ወለድ አለሙ እንዳሉ ከሆነ፤ ቤቶቹ የጥራት ችግር ሊኖርባቸው እንደሚችል አምነው፤ነገር ግን የመሰረተ ልማት አለመሟላት የእኛ ችግር አይደለም ብለዋል፡፡

የከተማው ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን እንዲሁም፤የአዲስ አበባ ከተማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢሮ፣ የውሃ እና የመብራት መስመሮች ላለመዘርጋታቸው የአካባቢው የመንገድ መሰረተ ልማት አለማለቁ እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡

መሳይ ገ/መድህን
መጋቢት 01 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.