ሰበታ ከተማ መንታ መንገድ ላይ ቆሟል

በቤትኪንግ የኢትዮጲያ ፕሪምየር ሊግ በመወዳደር ላይ የሚገኘው ሰበታ ከተማ ከ15 ጨዋታ 9 ነጥቦችን በመሰብሰብ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ተቀምጧል ፡፡

የፕሪምየር ሊጉ ሌሎች ቡድኖች ለሁለተኛ ዙር ዝግጅት እያከናወኑ ባሉበት በዚህ ወቅት ሰበታ ከተማ ድክመቱን ለማስተካከል ሁነኛ ጥረት እያደረገ አይደለም፡፡

የቡድኑ አስር ተጫዋቾች ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው በመግለጽ ቅሬታቸውን ለኢትዮጲያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስገብተዋል ፡፡

ገንዘቡ እስካልተከፈላቸው ድረስ ወደ ልምምድ እንደማይመለሱም አሳውቀዋል ፡፡

የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ምንዳ ከኢትዮ ስፖርት ጋር ባደረጉት ቆይታ የተፈጠረው ችግር እውነት መሆኑን አምነው መፍትሄ ለማግኘት ለክለቡ ቦርድ ጥያቄ ማቅረባቸውን እና ተጨማሪ በጀት እንዲፈቀድላቸው መጠየቃቸውን ተናግረዋል፡፡

ስራ አስኪያጁ ዘንድሮ ያልከፈሉት የሁለት ወር ደመወዝ ብቻ መሆኑን እና ተጫዋቾቹ እያነሱ ያሉት ክፍያ ዓምና የተጫዋቾች የደመወዝ ጣሪያ 50 ሺ ብር እንዲሆን ተወስኖ በነበረበት ወቅት ከጠረጴዛ ስር አድርገውት የነበረው ስምምነት ቀሪ ክፍያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል በውድድር ዘመኑ መጀመሪያ ለአጠቃላይ የውድድር ዘመኑ የክለቡ እንቅስቃሴ እንዲውል እስከ ዓመቱ መጨረሻ የሚበቃ ገንዘብ ተሰልቶ ወጪ ተደርጓል መባሉንም አስተባብለዋል፡፡

ክለቡ ያስቀመጠለቻውን ግብ ማሳካት አልቻሉም በሚል ከስራ የታገዱት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጉዳይ እልባት ሳያገኝ አዲስ አሰልጣኝ ስለመቅጠር እንደማያስቡም ተናግረዋል፡፡

ከጊዜያዊ አሰልጣኙ ብርሃን ደበሌ ጋር በቡድኑ ዙሪያ መወያታቸውን እና ያስፈልጋሉ የተባሉ ተጫዋቾችን መለየታቸውንም አሳውቀዋል ፡፡

ሆኖም አሁን ክለቡ የሚገኝበት የፋይናንስ ሁኔታ እንኳን አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ይቅርና የያዛቸውንም ተጫዋቾች በቅጡ ማስተናገድ እንዳይችል እንደገደበው ተናግረዋል፡፡

የቡድኑ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በቀጣዮቹ ቀናት ቦርዱ በሚወስነው ውሳኔ ላይ ተንጠለጠለ ይመስላል፡፡

አቤል ጀቤሳ
መጋቢት 06 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *