በኢትዮ ቴሌኮም እና ሳፋሪኮም መካከል በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እየተደረገ ያለዉን ድርድር በራሳቸዉ ለመፍታት እየሞከሩ ነዉ ብሏል የኢትዮጵያ ኮሚኒኬሽን ባለስልጣን ፡፡

የኢትዮጵያ ኮሚኒኬሽን ባለስልጣን በሁለቱ ኦፕሬተሮች መካከል እየተደረገ ያለዉ ድርድር ወደ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አለመምጣቱን እና ድርድሩንም በሁለቱ መካከል ለመፍታት እየተሞከረ መሆኑን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ባልቻ ሬባ ለኢትዮ ኤፍኤም ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ ኦፕሬተሮች በሶስት ጉዳዮች ላይ ይህም በመሰረተ ልማት መጋራት፣ በኢንተር ኮኔክሽን እና በ ሃገር ዉስጥ ሮሚንግ ላይ እየተደራደሩ እንደሆነ እና ድርድሩንም ወደ ማጠናቀቁ መድረሳቸዉንም እንረዳለን ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ ፡፡

ይህ ጉዳይ ወደ እኛ ቢሮ የሚመጣበት አግባብ በኮሚኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ እና በስሩ በተቋቋሙ የተለያዩ መመሪያዎች መሰረት ሲሆን ይህም ማለት ሁለቱ ኦፕሬተሮች ጉዳዩን በድርድር መፍታት ካልቻሉ፣ ወጪን መሰረት ባደረገ መልኩ፣ዉድድርን በሚያበረታታ መልኩ ከስምምነት ላይ መድረስ ካልቻሉ እና አንዱ ወገን ጉዳዩን ወደ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይዞ ከመጣ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ችግሩን አይቶ፣ መርምሮ መፍትሄ የሚሰጥበት አግባብ አለን ብለዋል፡፡

ለሃገር ዉስጥ ለሚቀርብ የትኛዉም አገልግሎት በብር ነዉ ክፍያ የሚፈጸመዉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ፣ በቴሌኮም የተለየ ባህሪይ ምክንያት ግን የተወሰነ መጠን ክፍያ በዶላር ሊሆን ይችላል፡፡

ሳፋሪኮም የኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ታወር ላይ የራሱን አንቴናዎች አምጥቶ ሲያስቀምጥ አንድ ለቦታዉ ሁለት ደግሞ ለኤሌክትሪክ ሃይሉ ይከፍላል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ደግሞ የኤሌክትሪክ ሃይል ቀንሶ ለሳፋሪኮም ሲያቀርብ ይህንን አገልግሎት ለመስጠት በስራ ላይ የሚዉሉት እንደ ባትሪ ፣ ጀነሬተር የመሳሰሉ ዕቃዎች ከዉጭ የሚገቡ ስለሆነ እነዚህን ዕቃዎች ለማስገባት የሚሆን የተወሰነ ገንዘብ በዶላር እንዲከፈለዉ ይፈልጋል ይህም ደግሞ በመሃከላቸዉ የመሰረተ ልማት መጋራት ላይ አለመስማማት እንዲኖር አድርጓል ተብሏል፡፡

እንደዚህ ዓይነት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችም የተሟሉ ስለሆነ ጉዳዩ ወደ እኛ ከመጣ የዳኝነት ሂደቱ የሚከናወን ይሆናል ብለዋል፡፡
መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም
እስከዳር ግርማ

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.