የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በጦርነት እና ግጭቶች ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚውል ከ134 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰብ መቻሏን አስታወቀች፡፡


የቤተክርስቲያኗ 52ኛ የጳጳሳት ጉባኤ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት በኢትዮጵያ በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር እና በኦሮሚያ ክልሎች በጦርነት እና ግጭቶች ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ ቤተክርስቲያን የበኩሏን እንድታደርግ አቅጣጫ አስቀምጧል።

ይህንኑ መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ የጳጳሳት ጉባኤው ጠቅላይ ጽ/ቤት የቤተክርስቲያን አጋር ድርጅቶችን እና ምእመናንን በማስተባበር ከ134 ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ መቻሏን ቤተክርስቲኗ አስታውቃለች፡፡

ይህንኑ የሰብዓዊ ድጋፍ ፕሮጀክት በይፋ የማስጀመር ሥነሥርዓት በነገው እለት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌልን ጨምሮ ሌሎች ብፁዓን የቤተክርስቲያኗ ጳጳሳት እና የቤተክርሰቲያኒቱ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ይከናወናል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የተፈጠሩትን ግጭቶች እና ሰብአዊ ቀውሶች በተመለከተም ምርመራ እና ጥናት እያደረገች እንደምትገኝ ቤተክርስቲያኗ አስታውቃለች፡፡

በኢትዮጵያ በሰሜኑ አካባቢ የነበረውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ያላለሰለሰ ጥረት ስታደርግ እንደነበረ ነው የተገለጸው፡፡

መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም
ሔኖክ ወልደገብርኤል

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *