የዬክሬን ፕሬዝዳንት በግራሚ የሽልማት ስነ ስርአት ሳይጠበቁ ተከስተዋል፡፡

የዬክሬን ፕሬዝዳንት በግራሚ የሽልማት ስነ ስርአት ሳይጠበቁ የተከሰቱ ሲሆን ዩክሬንን በምትችሉት ሁሉ ደግፉ ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል::

ትናንት ሌሊት በግራሚ የሽልማት ስነ ስርአት ማንም ባልጠበቀበት ቅፅበት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌኒስኪ ድንገት በቪዲዮ መልዕክት በትልቁ ስክሪን የተከሰቱ ሲሆን ስነ ስርአቱን ለሚከታተሉ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ተመልካቾች በምትችሉት መንገድ ሁሉ ደግፉን በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

መድረኩን እየመራ የነበረው ኮሜዲያንና የ “The Daily Show” አዘጋጅ ትሬቨር ኖዋህ ሙዚቃን ሁልጊዜም ሀይለኛ የሚያደርገው አንድ ነገር ለወቅቶች የሚሰጠው ምላሽ ነው፣ ጨለምተኛ ወቅቶች ላይ እንኳን ለብሩህ ነገ ተስፋ እንድናደርግ ስሜታችንን ከፍ የማድረግ ሀይል አለው ብሏል፡፡

በአሁን ሰአት ማንም እንደ ዩክሬን ህዝብ ትንሽ ተስፋን ሊጠቀም የሚችል የለም ሲል ዜሌኒስኪን አስተዋውቋል፡፡
ዜሌኒስኪ ፤ ከጦርነት በላይ ከሙዚቃ የተቃረነ ምን ሊኖር ይችላል፤ ጦርነት የሚገለፀው በወደሙ ከተሞችና በተገደሉ ሰዎች ዝምታ ነውና ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ልጆቻችን የሚተኮሱ ከዋክብትን ሳይሆን የሚተኮሱ ሮኬቶችን ነው እየሳሉ ያሉት፣ 400 ህፃናት የተጎዱ ሲሆን 153 ቱ ህፃናት ደግሞ ሞተዋል፤ ድጋሚ ሲስሉ አናያቸውም ብለዋል ዜሌኒስኪ፡፡

ወላጆቻችን በቦምብ ከተደበደቡ መጠለያዎቻቸው ጠዋት ሲነቁ በህይወት በመኖራቸው ይደሰታሉ፤ ውዶቻችንና ቤተሰቦቻችን በድጋሚ አንድ ላይ መሆን አለመሆናችንን እርግጠኛ አይደሉም፡፡
በቀጣይ ማን ይዳን ማን በዘላለማዊ ዝምታ ይቆይ የሚለውን አናውቅም፤ ብለዋል፡፡

ሙዚቀኞቻችን ቶክሲዶ ሳይሆን የጦር ትጥቅ ለብሰዋል፤ በሆስፒታሎች ለቆሰሉትና ለማይሰሟቸው ጭምር እያዜሙ ነው፡፡

ለመኖር፣ለማፍቀርና ለመፈቀር፣ ለመደመጥ፣ ለነፃነታች እንታገላለን፡፡

በመሬታችን ላይ ወራሪዋንና በቦምቦችዋ አስከፊ ዝምታ በከተሞቻችን ላይ የፈጠረችዋን ሩሲያ እየተዋጋን ነው፤ ብለዋል፡፡

ይሄን ዝምታ በሙዚቃዎቻችሁ ሙሉ! ስለዚህ ጦርነትም እውነታውን ተናገሩ! በምትችሉት መንገድ ሁሉ ደግፉን ሲሉ ዜሌኒስኪ ልብ የሚነካ ንግግራቸውን ደምድመዋል፡፡
ንግግሩን ተከትሎ ጆን ሌጀንድ ሲዩዛና ኢግሊዳን ከተባለችው ዩክሬናዊ ሙዚቀኛ ጋር “Free.” (ነፃነት) ሲል ያዘጋጀውን ሙዚቃ አቅርቧል፡፡

ምንጭ፡- ዋሽንግተን ፖስት

በሔኖክ አስራት

መጋቢት 26 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *