ዶ/ር ደብረጺሆን ገ/ሚካኤል እና ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 37 ተከሳሾች በጋዜጣና በEBC ጥሪ እንዲደረግላቸው ታዘዘ፡፡

=======#=======
ዶ/ር ደብረጺሆን ገ/ሚካኤል እና ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 37 ተከሳሾች በጋዜጣና በEBC ጥሪ እንዲደረግላቸው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረሽብርና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት አዝዟል።

በዶ/ር ደብረፂሆን የክስ መዝገብ በሽብር ወንጀል ከተከሰሱ 62 ተከሳሾች ውስጥ ስብአት ነጋ፣ ሙሉ ገብረእግዛብሔርን ጨምሮ ስድስት የህውሐት አመራሮች በመንግስት ክሳቸው መቋረጡ ይታወሳል።

በዛሬው ቀጠሮ ፍርድ ቤት የቀረቡት ኬሪያ ኢብራሂም፣ ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ እና ዶ/ር አብርሐም ተከስተን ጨምሮ 17 ተከሳሾች በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።ቀሪዎቹ የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደብረጺሆን ገ/ሚካኤል፣ የህወሃት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 37 ተከሳሾች ግን በቁጥጥር ሥር ያልዋሉ ተከሳሾች ናቸው።

ፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ እንዲቀርቡ ፌደራል ፖሊስ መጥሪያ እንዲያደርስ ያዘዘ ቢሆንም፤ ፖሊስ ካለው የጸጥታ ሁኔታ አንጻር ለተከሳሾቹ መጥሪያ ማድረስ አለመቻሉን በዛሬው ቀጠሮ መልስ ሰጥቷል።

ከሳሽ ዓቃቢህግም ተከሳሾቹ ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግ ጠይቋል።
በጠበቆች በኩል በጋዜጣ ጥሪው ላይ መቃወሚያ አልቀረበም።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረሽብርና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ለ37 ተከሳሾች በጋዜጣና በኢትዮጲያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) ጥሪ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ መሰጠቱን አዲስ ማለዳ ዘግቧል፡፡

በጋዜጣ ጥሪውን የማይቀርቡ ከሆኑ በሌሉበት ለመመልከት ውጤት ለመጠበቅ ለግንቦት 8 ቀን 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *