“አማራ ክልላዊ መንግስት በመነሳት የጦር መሳሪያ የታጠቁ ኃይሎች በኃይል በመጣስ ጦርነት አውጀው የመሬት ወረራና የግዛት ማስፋፋት ተግባር ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ “ ኦፌኮ

ኦፌኮ መንግስት ሰሞኑን በአዲስ መልኩ ያወጀው ዘመቻ በጥቂቱ ፈንጥቆ የነበረውን የሰላም ጭላንጭል መልሶ የሚያደበዝዝ፤ኦሮሚያና አገሪቱን ለተጨማሪ አደጋ የሚያጋልጥ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ የማይሰጥ ነው ብሏል

በሁለቱ አካላት መካከል ያለው ግጭት ፖለቲካዊ መንስዔ ያለው ሲሆን መፍትሄውም ፖለቲካዊ መሆን አለበት ብሎ እንደሚያምንም አሳውቋል፡፡
በአጎራባች የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች መካከል የሰላምና ፀጥታ ችግር እየተባባሰ ነው ያለው መግለጫው፣ ከሰሞኑ ይፋ እየተደረጉ ካሉ ዘገባዎች መረዳት እንደሚቻለው ከአማራ ክልላዊ መንግስት በመነሳት የጦር መሳሪያ የታጠቁ ኃይሎች በተለያዩ ስፍራዎች በኩል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትን የታወቀ ወሰን በኃይል በመጣስ ጦርነት አውጀው የመሬት ወረራና የግዛት ማስፋፋት ተግባር ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ ብሏል ኦፌኮ በመግለጫው ፡፡

እነዚህ ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎችን በመግደል፤አርሷደሮችን ከመሬታቸው በማፈናቀል ክልሉን ወደማያባራ የግጭት ቀጠና እየለወጡት እንደሚገኙ ፣ በተለይም ይህ የጦር ዘመቻና የመሬት ወረራ በምስራቅ ወለጋ፤ሆሮ ጉድሩ ወለጋ፤ሰሜን ሸዋ፤ ምዕራብ ሸዋና በምስራቅ ሸዋ ዞኖች፤ በተቀናጀ አኳኋን እየተካሔደ እንደሚገኝ ከአባሎቻችን እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ለመረዳት ችለናል ብሏል፡፡

ታጥቀው ወረራ እያካሔዱ ባሉ የአማራ ክልል ኃይሎች በሚዲያ የሚሰጡት መግለጫም ይህንኑ ያረጋግጣል ብሏል ፡፡
ይህን ወረራ የሚያካሂዱት ከክልሉ መንግስት እውቅና ውጪ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ “ጽንፈኛ” ኃይሎች ናቸው ቢባልም ይህ እውነት እንዳልሆነ የሚያመላክቱ ማስረጃዎች አሉ ካለ በኃላ፣ እንዲህ ያለው አሰራር ህገመንግስቱን ከመፃረር አልፎ የሁለቱ ክልሎች ወንድማማች ህዝቦች ወደለየለት ጦርነት እንዲገቡ በር የሚከፍት መሆኑን ኦፌኮ አበክሮ ያስጠነቅቃል፡፡

ይህ በጥላቻ ፕሮፓጋንዳ እየታገዘ የሚካሔደው የመሬት ወረራና የግዛት ማስፋፋት ዘመቻ ቀድሞውንም ባልሻረ ቁስል ላይ ጨው በመነስነስ የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት ወደከፋ የመጠፋፋት ጦርነት ሊገፋ እንደሚችል ሁለቱም ወገኖች ሊገነዘቡ ይገባል ሰል አገልጻል፡፡

በሁለቱ ክልሎችና እነዚህ ትልልቅ ህዝቦች መካከል የሚደረገው ጦርነት አገሪቱንም ለብተና፤ የአፍሪካን ቀንድ ደግሞ ለከፋ አለመረጋጋት የሚያጋልጥ መሆኑ ታውቆ ይህ ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም ኦፌኮ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል፡፡

ሚያዝያ 03 ቀን 2014 ዓ.ም

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.