የሲሚንቶ የቅዳሜና እሁድ ገበያ (” ሰንዴይ ማርኬት “ ) ሊጀመር መሆኑ መንግስት አስታወቀ፡፡

ጣራ የነካው የሲሚንቶ ዋጋ ለማረጋጋት መንግስት የቅዳሜና እሁድ ገበያ (” ሰንዴይ ማርኬት “ ) ሊጀመር እንደሆነ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሀመድ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውል ባልታወቀ ምክንያት የሲሚንቶ ዋጋ በእጥፍ መጨመሩን የተናገሩት ሚንስትሩ ይህንን ለመቆጣጠር መንግስት የተለያዩ የቁጥጥር ስራዎች እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ለሲሚንቶ ዋጋ መናር እንደ ምክንያት ያስቀመጡት አቶ ሀሰን መሀመድ የግብአት እጥረት፣ ህገወጥ ደላሎች፣ የጥቅም ትስስት የፈጠሩ ነጋዴዎች የሚፈጥሩት አሻጥር እና በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ሁኔታዎች ናቸው ብለዋል፡፡

መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶችን ለተጠቃሚው በቀጥታ ለማድረስ የተጀመረው የቅዳሜ እና እሁድ ገበያ በርካታ ስኬቶች ታይተውበታል ያሉ ሲሆን የሲሚንቶ ገበያም ለመጀመር ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
ህገወጥ ደላሎችን ለመቆጣጠር እና ተጠቃሚው በቀጥታ የሲሚንቶ ምርት ከአምራች ድርጅቶች የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ነው የተባለው፡፡

በሀገሪቱ ከ18 በላይ የሲሚንቶ አምራቾች ቢኖሩም በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ የሚገኙ ከአራት ወይም ከአምስት አይበልጡም ሲሉ ነው ሚኒስትር ዴኤታው ለኢትዮ ኤፍ ኤም የተናገሩት፡፡

ሚያዝያ 05 ቀን 2014

ሔኖክ ወ/ገብርኤል

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *